የመከላከያ ሰራዊቱ ወልድያን ለቆ እንዲወጣ ህዝቡ ያቀረበው ጥያቄ እየበረታ መሆኑ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና 

አመታዊ ክብረ በዓሉን እንደወትሮው በዝማሬና በጭፈራ ሲያከብሩ የነበሩ ወጣቶች ላይ ተኩስ ከፍተዋል የተባሉ የመንግስት ወታደሮች ከወልዲያ ለቀው እንዲወጡ ህዝቡ መጠየቁ ተሰምቷል።

የቃና ዘገሊላ በአልን ለማክበር በወጡ የወልድያ ህዝብ ላይ የመንግስት ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ የተቀሰቀሰው ግጭት በሰኞ እለት ጋብ ብሎ እንደዋለ ቢነገርም ወታደሮች ከቦታው ይልቀቁ የሚል ጥያቄ እየበረታ እንደሆነ ተገልጿል።

ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በእሁድ እለት ወደ ወልድያ በማቅናት ከወጣቶችና ከህዝቡ ጋር መወያየታቸውን ከክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ መጠይቅ መናገራቸው ይታወሳል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዚሁ የቴሌቭዥን ቃለመጠይቃቸው ወጣቱ የፖለቲካ ጥያቄዎች እና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን እንዳነሳ ሲጠቁሙ የመከላከያ ሰራዊቱ ከወልድያ ለቆ ይውጣ በማለት ህዝቡ ያነሳውን ጥያቄ ግን ሸፋፍነው አልፈውታል።

ታቦትን አጅበው በነበሩ የወልዲያ ህዝብ ላይ ተኩስ ከፍተው በርካታ ሰዎችን ያቈሰሉትና የገደሉት የመንግስት ታጣቂዎች በዛሬው እለት ቁጥራቸውን ጨምሮ በከተማው መታየታቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል።

የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ዓመታዊ በአል ላይ በወሰዱት እርምጃ በትንሹ 7 ሰዎች መገደላቸውን አቶ አማረ ጎሹን ጠቅሶ ዘ ኒዮርክ ታይምስ “7 die at Ethiopia’s Epiphany in clashes with security forces” በሚል ርእሱ ለአለም አስነብቧል።

ዘዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ “7 die at Ethiopia’s Epiphany in clashes with security forces” በሚል ርእስ በወልዲያ ህዝብ ላይ የደረሰውን ግድያ በመዘገብ የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን እና  የተቃዋሚ አባላትን እያሰረ እንደሆነ የመብት ተከራካሪዎች ክሳቸውን እያሰሙ እንደሚገኙ አስፍሯል። ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ መንግስትን አሁንም በአጋርነት ኣና በወዳጅነት የምታይ መሆኗን አስነብቧል።

ቢቢሲ በእንግሊዘኛው የዜና ዘገባው የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በአልን ለማክበር በወጡ አማኞች ላይ በከፈቱት ተኩስ በትንሹ 5 ሰዎችን ገድለው በርካታ ሰዎችን ማቁሰላቸውን ለአንባቢያን በማቅረብ አገዛዙን በይፋ የመቃወም እንቅስቃሴው 3 አመታትን ያስቆጠረ እንደሆነ በመጥቀስ አገዛዙ ከኦሮሚያና ከአማራ ህዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው እንደሆነ አትቷል።

የቃና ዘገሊላ በዓልን ታቦትን በማጀብ በዝማሬና በጭፈራ ሲያከብሩ በመንግስት ሃይሎች በተወሰደ እርምጃ ህይወታቸውን ላጡ ንፁኋን የወልዲያ ሰዎች ነፍስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መፅናናትን እንመኛለን።

Source Article from http://amharic.abbaymedia.info/archives/41604