“እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ናት” ዶናልድ ትራምፕ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ቃል እንደገቡት እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ እንደሆነች ዛሬ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል።

በዚህም መሰረት እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ እንደሆነች እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ አገር ዩናይትድ ስቴትስ ሆናለች።

እየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን እውቅና መስጠት ትክክል እንደሆነና እውነታንም መቀበል እንደሆነ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ እንደሆነች እውቅና በመስጠታቸው ለረዥም አመታት ሲጠበቅ ለነበረው ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲንም ከቴላቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንዲዘዋወርም ትእዛዝ መስጠታቸውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናግረዋል።

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሃሙድ አባስ  ውሳኔውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ እየሩሳሌም ዛሬም ሆነ ለዘለላም የፍልስጤም ዋና ከተማ ትሆናለች በማለት የትራምፕን ውሳኔን ተቃውመዋል።

የፍልስጤሙ ሃማስ በበኩሉ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ የሲኦልን በር ይከፍታል በማለት ዛቻውን ሰንዝሯል።

ግብጽ፣ ኢራን እንዲሁም ፈረንሳይ ከአለም አቀፉ ህግ የተቃረነ ውሳኔ እንደሆነ በመጥቀስ ፕሬዝዳንት ትራምፕን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።

የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ የነበሩት ኮፊ አናንም በውሳኔው እንዳዘኑና በእየሩሳሌም ጉዳይ የፍልስጤምም ሆነ የእስራኤል ጥቅም  ካልተከበረ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ማምጣት እንደማይቻል በቲውተር መልክታቸው አሳውቀዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ፕሬዝዳንት ትራምፕን በማመስገን ሌሎች የአለም አገራትም ኤምባሲያቸውን ወደ እየሩሳሌም እንዲያዘዋውሩ ጠይቀዋል።

በውሳኔው የተበሳጩ ፍልስጤማውያን የፕሬዝዳንት ትራምፕንና የቤኒያሚን ኔታኒያሁን ምስሎች እንዲሁም የእስራኤልን ባንዲራ ሲያቃጥሉ ተስተውለዋል።

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንትን፣ የቱርክ ፕሬዝዳንት፣ የብርታኒያ ጠቅላይ ሚንስትር ፣ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ የአረብ ሊግ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ሲያሰሙ እንደነበረ ይታወሳል።

ምስራቅ እየሩሳሌምን ስድስት ቀናት በቆየው ጦርነት በ 1967እኤአ እስራኤል በቁጥጥሯ ስር ብታውልም በአለም አቀፍ እውቅና ግን ሳያገኝ የቆየ እንደሆነ ታሪክ ያሳያል።

 

Source Article from http://amharic.abbaymedia.info/archives/39855