በኢትዮጵያ የተገደለውን ጀርመናዊ ተከትሎ ካናዳና ብርታኒያ የጉዞ ማስጠንቀቂያ አወጡ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ 

የኤርታሌ እሳተ ገሞራን ለመጎብኘት ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ ጀርመናዊ መገደሉን የጀርመን መንግስት ማረጋገጫ መስጠቱን ተከትሎ የተለያዩ አገራት የጉዞ ማስጠንቀቂያ ማውጣታቸው ታወቀ።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮም ጥቃቱ እንደተፈጸመና የጀርመናዊው ጎብኚ ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።

ጀርመናዊው ጎብኝ በጥይት ተመትቶ ሲገደል ከጎብኝዎች ጋር የነበረ ኢትዮጵያዊ ሹፌር ቆስሏል ወይም ሞቷል ተብሏል። የትኛው ትክክል እንደሆነ የሚያረጋግጥ ዜና ግን ይህ ዘገባ እሰከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ አልተገኘም።

የብርታኒያ መንግስት ይህን የጀርመን ዜጋ መገደል ዜና በመመርኮዝ ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ዜጎቿ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ አስተላልፋለች። ጀርመናዊው ዜጋ በተገደለበት አከባቢ  የመንግስት ወታደሮች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ በመጠቆም በአከባቢው የሚገኙ ዜጎቿ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ብርታኒያ በተጨማሪ አስጠንቅቃለች። የካናዳ መንግስትም እንደዚሁ ዜጎቹ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል። ዜጎች የደናክል በረሀ እና ኤርታሌ እሳተ ገሞራን ለመጎብኘት  የያዙትን እቅድ እንዲሰርዙና ወደ አከባቢው ከመጓዝ እንዲቆጠቡም የካናዳ መንግስት ተጨማሪ መልክት አስተላልፏል።

ከአምስት አመት በፊት በዚሁ ክልል በተፈጸመ ጥቃት 5 የውጭ ዜጎች መገደላቸውን  በማስታወስ የአሁኑን ግድያና ጥቃት የፈጸሙትን በቁጥጥር ስር ለማዋል መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።

 

Source Article from http://amharic.abbaymedia.info/archives/39847