የጎንደርና ጎጃም ሕብረት የቡኖ በደሌን ጭፍጨፋ አወገዙ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

የጎንደር ህብረትና አቻው የጎጃም አለም አቀፍ ትብብር የዋሽንግተን ዲሲ 16ኛ ጉባኤ በኢሉባቦር ቡኖ በደሌ ለተጨፈጨፉት እና በጎንደርና ጎጃም ለተገደሉት ንጹሃን የሻማ ጸሎት ያደረጉ ሲሆን የቡኖ በደሌን ጥቃት በጽኑ ማውገዛቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ዋና ዓላማውን በህወሃት መራሹ መንግስት በጎንደር፣ በጎጃምና አሁን ደግሞ በኢሉባቦር ቡኖ በደሌ በግፍ ለተገደሉት ጸሎት ለማድረግ እንደሆነ ወ/ሮ ሊያ ፈንታ ገልጻ በኢሉባቦሩ ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ድርጊቱ በዘረኝነት ምክንያት በስልጣን ላይ ባለው ስርዓት በጎ ፍቃድና ይሁንታ እንደተፈጸመ ገልጻ ተጠያቂውና የድርጊቱ መሪ ስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ነው በሚል አቃም ድርጊቱን ክፉኛ ማውገዛቸውን ተናግራለች።

ዘረኝነትን እናወግዛለን፣ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ለጥቃት ሊዳረጉና ህልውናቸው እንዲጠፋ መደረግ የለበትም ያሉት ሁለቱ ድርጅቶች በዘር ምክንያት እየደረሰ ያለውንም ጥቃት በጋራና በአንድነት መመከትና መታገል አለብን ማለታቸውን ወ/ሮ ሊያ ትናገራለች።

በሁለቱ ህዝቦች መካከል የጠላትነትን ግንብ በመገንባት ቦዝኖ የማያውቀው የህወሃት መራሹ መንግስት ዛሬም በአማራውና በኦሮሞው መካከል የተፈጠረውን ጥምረትና አንድነት ለማፈራረስ መሰሪ በሆነ ሁኔታ በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ግጭት የተነሳ በማስመሰል በኦሮሚያ ክልል በተለይም በሰሜን ሸዋ፣በጂማና ብሎም በኢሉባቦር በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ በስርዓቱ ሃይሎች እውቅና ስር ጥቃት እየተፈጸመ ነው በማለት ኮንነው በሁለቱ ህዝቦች ትብብርና አንድነት ይህንን የጋራ ጠላት መታገል ይገባናል ሲሉ ጥሪም አድርገዋል።

በስነስርዓቱ ላይ ከጎንደር ህብረት አቶ አንተሁን እጅጉ የማህበሩ የዲሲ ጸሃፊ ፣በጎጃም ዓለም አቀፍ ትብብር በኩል ደግሞ አቶ ዝናህ ምንያህል የተገኙ መሆናቸውን ወ/ሮ ሊያ ገልጻ ከሃይማኖት አባቶች በኩል ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ መምህር ፍሬሰው ገድሉ እና ከሙስሊሙ ማህበረሰብ በኩል ደግሞ ኃጂ ነጂብ በስፍራው በመገኜት ለሰማእታቱ ጸሎት ማድረጋቸውን እና ዘረኝነትንም ለህዝብ እና ለአንዲት ሀገር ጠንቅ ነው በማለት ማውገዛቸውን ገልጻለች።

በሳምንቱ መጨረሻ በኢሊባቦር [ኢሉ-አባቦራ] በቡኖ በደሌ በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ በተፈጸመ ኢሰብዓዊና አረመኔያዊ ጥቃት ከ11በላይ ሰዎች በግፍ የተገደሉ፣ ከ50በላይ ቤቶች የተቃጠሉና በመቶ የሚቆጠሩት ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በየፖሊስ ጣቢያ እና በጫካ ተጠልለው እንዳሉ ይታወቃል።

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/37589