አገዛዙ ህዝባዊ አመጹን ማስቆም እንደማይቻለው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን በእስር የተነጠቀው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ በኢትዮጵያውያኖች ላይ እየፈጸመ ያለውን ድርጊት በጽኑ ኮንኗል።

ኢትዮጵያውያኖች በተለያዩ ከተሞች በጀግንነት ወደ አደባባይ በመውጣት መንግስትን በመቃወምና በእስር የሚገኙትን ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ያቀረቡት ጥያቄዎች ከአገዛዙ በኩል መልስ ያለማግኘቱንም ኮንግረሱ በመግለጫው ገልጿል።

ህዝቡ ያነሳውን ጥያቄ መንግስት በአግባቡ እንዲመልስና በአገሪቷ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን ከማደፍረስ እንዲቆጠብም ኦፌኮ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠይቋል።

መንግስት ህዝቡ ላይ ያደረሰውን በደል በግልጽ ካላሳወቀና ሰላማዊ መፍትሄዎችን ለማምጣት ጥረት ካላደገ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እየታየ ያለውን ህዝባዊ አመጽ ማስቆም እንደማይችልም ገልጿል።

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የተፈጠረውን ግጭት አገዛዙ የህዝቡን ጥያቄዎች ላለመመለስ ሆን ብሎ የፈጠራቸውና እንዲባባሱም እያደረጋቸው እንደሆነ ኮንግረሱ ጠቅሷል።

ለመቶዎች ህይወት መጥፋትና ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን የዚህን ግጭት መነሻ ለማጣራት ሰፊ ጊዜ እንደሚያስፈልገው መንግስት ማሳወቁ ይታወሳል።

በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ግጭት ህዝቡ ከፖለቲከኞች ከእስር መፈታት በተጫማሪ በህውሃት የበላይነት የሚመራው አገዛዝ ከስልጣን እንዲወርድ ያቀረበውን ጥያቄ መንግስት ለማድበስበስ የተጠቀመበት ስልት ነው በማለትም ኦፌኮ በመግለጫው ከሷል።

ነዋሪነታቸውና ስራቸው በኦርሚያ ያልሆኑ ግለሰቦች በየሰልፉ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመመሳሰል በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው ታውቋል ሲል ኦፌኮ በመግለጫው አስፍሯል።

እንዚህ ግለሰቦች አገዛዙ የከለከላቸውን አርማዎች ሆን ብለው በማውለብለብ እንዲሁም ሁከት በመፍጠር አገዛዙ ሰላማዊ ሰልፉን ህገወጥ እንደነበረ ለማሳየት የሚያደርገውን ሴራ ሲያግዙ እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

ሰላማዊ ሰልፉን ወደ ብጥብጥ እንዲያመራና ህይወት እንዲጠፋ ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች ማንነትና ፎቶዎች እንዲሁም የቪዲዮ ምስሎች ለማስረጃነት በእጁ እንደሚገኙ ኦፌኮ ተናግሯል።

የመንግስት ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በወሰዱት እርምጃ ለጠፋው የሰዎች ህይወት እንዲሁም በሶማሌና ኦሮሚያ ለተፈጠረው ግጭት የተሰማውን ሃዘን ኦፌኮ በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/37445