በኦሮሚያ ሕዝባዊ አመጽ ተቀጣጥሏል-ወያኔ ውረድ

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

በአብዛኛው የኦሮሚያ ክፍል ሕዝባዊ ዓመጽ በመነሳቱ ከፍተኛ ትእይንተ ህዝብ ሲካሄድ መዋሉን ማወቅ ተችላል።

በተነሳው ኦሮሚያ አቀፍ ህዝባዊ አመጽ የህወሃት መራሹ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ብሶቱን ለማሰማት በወጣው ህዝብ ላይ ጥይት መተኮሳቸው ታውቋል። በሻሸመኔ አራት ሰው በታጣቂዎች መገደላቸው ተገልጿል።

በምእራብ ኦሮሚያ አምቦ፣ ነቀምት፣ ጉዱሩ፣ ጊንጪ፣ ቡራዩና ሆሎታ ከተሞች በተካሄደ ህዝባዊ ተቃውሞ በእስር እየተሰቃዩ ያሉት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አመራር አባላት ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል። በእስር እየተሰቃዩ ያሉት የድርጅቱ አመራር አባላት ፕ/ር መረራ ጉዲና እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሁሉም ከእስር በአስቸካይ ይፈቱ በማለት ሰልፈኛው ጠይቋል።
በምስራቅም በኩል በሻሸመኔ፣ በአዳባ፣ በባሌና በምስራቅ ሐረርጌ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ከተሞቹን አጥለቅልቆት ውሏል። የመንግስትን ከስልጣን መነሳት በይፋ ሲጠይቅና ሲያስተጋባ ውሏል።

በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በህዝቡ ላይ የሃይል እርምጃ መውሰዳቸውም ተገልጿል።

ህወሃት መራሹ መንግስት ፕ/ር መረራ ጉዲናን ለመፍታት ሽማግሌ መላኩን እና ፕ/ሩ አጥፍቻለሁ ብለው ይቅርታ እንዲጠይቁ መጠየቁን በትናትናው ዘገባችን የገለጽን ሲሆን ፕ/ሩም ላላጠፋሁት ጥፋት ይቅርታ አልጠይቅም ማለታቸውንም መዘገባችን አይዘነጋም። በዚህ በኦሮሚያ አቀፍ በሆነው ህዝባዊ ዓመጽ ላይ ጎልቶ እየተደመጠ ያለው የህዝቡ ጩኸት ወያኔ ውረድ የሚል የስርዓት ለውጥ የሚጠይቅ እንደሆነ መረዳት ተችሏል።

በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተወሰደው እርምጃ የተጎጂዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ተፈርቷል።

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/37149