ከሊቢያ ስደተኞችን የጫነ ጀልባ ሰጥሞ ከ 50 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ባሳለፍነው አርብ 100 ስደተኞችን ከምእራብ ሊቢያ የባህር ዳርቻ በመጫን ወደ አውሮፓ ለማሻገር ሲሞክር የነበረ ጀልባ ባጋጠመው የነዳጅ እጥረት በመስጠሙ ምክንያት በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ተዘገበ።

ቢያንስ ወደ 50 የሚጠጉ ስደተኞች በተከሰተው አደጋ ሰጥመው ሳይሞቱ እንዳልቀረም ተገልጿል።

ከዚህ አደጋ የተረፉት ሰዎች በቁጥር 35 እንደሆኑ የሊቢያ የባህር ሃይል ባለስልጣናት እየተናገሩ ይገኛሉ።

በጀልባው መስጠም ህይወታቸውን ያጡ ስደተኞች ዜግነት ማወቅ ባይቻልም የተረፉት ግን በአብዛኛው ከሳሃራ በረሃ በታች ከሚገኙ አገራት እንደሆኑም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

አፍሪቃውያን እጅግ ፈታኙን የሜዲትራኒያን ባህርን በማቋረጥ ወደ አውሮፓ የሚያደርጉት ስደት ለማስቆም ሃያላን የአውሮፓ አገራት ከሊቢያ መንግስት ጋር ስምምነት መፈጸማቸው ይታወሳል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባሳለፍነው ወር ከጣሊያን ከጀርመንና ከስፔን አቻቸው ጋር በመሆን ጦርነትን፣ አምባገነናዊ ስርአትን አሊያም ድህነትን የሸሹ አፍሪቃውያን ወደ አውሮፓ ተሰደው እንዳይመጡባቸው  ሲመክሩ እንደቆዩም ይታወቃል።

በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት አፍሪቃውያንን ስደተኞች በተመለከተ የአውሮፓ ህብረት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ኮንኗል።

 

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/36084