በጀርመን ፍራንክፈርት ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ቆንስላ ፊት ለፊት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ዋሉ

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቷ እየፈጸመ ያለውን የመብት ረገጣና አፈና በመቃወም በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በመስከረም 11 ቀን 2010 ዓ.ም በአሜሪካ ቆንስላ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን በማውለብለብ ህወሃት በበላይነት የሚመራው መንግስት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍ በከፍተኛ ድምጽ ሲያወግዙ ውለዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እጅግ አሰቃቂ የሚባል የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ የሚገኘውን ይህን የህወሃት አገዛዝ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ህብረት ከመደገፍ እንዲቆጠቡም ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ሲጠይቁ ተሰምተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በንጹሃን ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን አፈና፣ ግድያ፣ የመብት ረገጣና፣ የአምባገንነት አገዛዝን የሚተነትንና በአገዛዙ ላይ ሊወሰድ የሚገባ እርምጃ የያዘው H.R. 128 በመባል የሚታወቀውን ረቂቅ ሰነድ የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት እንዲያጸድቀውም ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።

ይህ ረቂቅ ህግ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ድጋፍ አግኝቶ ተግባራዊ እንዲሆን የሚጠይቅም ደብዳቤ የሰልፈኞቹ ተወካዮች ለቆንስላው እንዳስገቡም ገልጸዋል።

የነጻ ፕሬስ አፈና እንዲሁም ጋዜጠኞች በስልጣን ላይ ባለው የህወሃት አገዛዝ ለእስር መዳረግ፣ መሰቃየትና መሰደድንም  በጀርመን ፍራንክፈርት ጎዳና የወጡ እነዚህ ሰልፈኞች በጽኑ ሲኮንኑ ተደምጠዋል።

በእስር ላይ እየማቀቁ የሚገኙትን ጋዜጠኞች፣ የመብት ተከራካሪዎች፣ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ መንግስት በአፋጣኝ በነጻ እንዲለቅም በመጠየቅ ድምጻቸውን ሲያሰሙ አርፍደዋል።

የጋዜጠኛነት ሞያ  ሽብርተኛ አያስብልም በሚል መፈክር በኢትዮጵያ ከታሰሩት ጋዜጠኞች መካከል እነ እስክንድር ነጋን፣ ውብሸት ታዬን፣ ተመስገን ደሳለኝን እና ሌሎችንም በመጥቀስ ከእስር እንዲለቀቁ ጥያቄያቸውን በጎላ ድምጽ ሲያስተጋቡም ተደምጠዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት ለህወሃት አገዛዝ የሚሰጠው የገንዘብ እርዳታ በአገሪቷ ላይ የሚፈጸመውን የመብት ረገጣ እንደመደገፍ ይቆጠራል በማለትም ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል። 

የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ከማስፋፋቱ  በፊት በአገሪቷ የህግ የበላይነትና የመብት መከበር እንዲቀድም የሚደረገውን ተጋድሎ ሊደግፍ እንደሚገባ  ኢትዮጵያውያኑ በሰልፉ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል።

በስልጣን ላይ ባለው የህወሃት አገዛዝ ከታሰሩት ጋዜጠኞች በተጨማሪም እነ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ኮሎኔል ደመቀ፣ አንዳርጋቸው ጽጌ እና ሌሎች ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስትና የአውሮፓ ህብረት በአገዛዙ ላይ ጫና እንዲያሳድሩበት ሰልፈኞቹ ሲጠይቁም አርፍደዋል።

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በአሜሪካ ቆንስላ ፊት ለፊት በተደረገው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያኖቹ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ እንዲሁም በጀርመንኛ ቋንቋዎች መፈክራቸውን በጎላ ድምጽ ሲያስተጋቡ ውለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በእንግሊዝኛና በጀርመንኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው በኢትዮጵያ ያለውን የመብት ረገጣ፣ የዲሞክራሲ እጦት፣ የነጻ ፕሬስ አፈና፣ ግድያ፣ እስራት እና በዚህ ምክንያት የሚከሰተውን የዜጎች ስደትን የሚተነትኑ በራሪ ወረቀቶች መበተናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ይህን ሰልፍ የጠራውና በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ በሙሉ ሃላፊነት ሲንቀሳቀስ የነበረው የፍራንክፈርት ግብረ ሃይል በጀርመን ከሚገኙ የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክስ ማህበር ጋር በመተባበር እንደሆነ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

 

 

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/36068