የኬኒያ ምርጫ ቦርድ ፕሬዚዳንቱን አሸናፊ ብሎ ሊያውጅ በተዘጋጀበት ሰዓት ተቃዋሚው እራሱን አሸናፊ ነኝ እንዳለ ነው

አባይ ሚዲያ
በወንድወሰን ተክሉ

ኬኒያ ለ5ኛ ቀን ዛሬም በከፍተኛ ውጥረትና ስራ አልባ ሆና ውላለች። የሀገሪቱ ምርጫ ቦርድ ከአንድ ሰዓት በhኋላ የምርጫውን አሸናፊ ለማወጅ በገለጸበት ወቅት የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ ኢዮቤሊዩ ደጋፊዎች ደስታቸውን ለመግለጽ በኬ አይ ሲ ሲ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ማእከል ተዘጋጅተው ባሉበት ሰዓት የተቃዋሚው ናሳ ደጋፊዎች ደግሞ በአንጻሩ ለዓመጽ ተዘጋጅተው ተግኝተዋል።

ቦማስ ኦፍ ኬኒያ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውጤት መግለጫ ማእከል በዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች፣ በኮር ዲፕሎማቲኮች፣ በፓርቲ ተወካዮችና በታዛቢ ልኡካን ቡድኖች ተጨናንቋል። የተቃዋሚው ናሳ መሪዎች ራይላ ኦዲንጋን ጨምሮ አብዛኞች ቀኑን ሙሉ ከምርጫ ቦርድ ጋር በቦማስ ኦፍ ኬኒያ በር ዘግተው ሲመክሩ ከቆዩ በኋላ ከሁለት ሰዓት በፊት ስፍራውን ለቀው ሄደዋል።

ሆኖም ከመሄዳቸው በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በምርጫ ቦርድ ሰሌዳ ላይ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታን በ8,190,019 ድምጽ 54.20% መሪነትን የሰጠና ተቀናቃኙን ራይላ ኦዲንጋን በ6,787,127 ድምጽ 44.91% የተገለጸውን እንደማይቀበሉ ገልጸው ተለይተዋል።

ተቃዋሚዎች ተሰርቀናል የሚሉትን ለመፍታት የምርጫ ቦርዱ አጠቃላይ ዳታ ቤዝ ለተቃዋሚዎችና ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት መሆን አለበት ብለዋል።

የኬኒያ መገናኛ ብዙሃን ህብረተሰቡን በማራጋጋት ስራ ተጠምደው ታይተዋል። ተቃዋሚው ትናትና እራሱን አሸናፊ ነኝ ብሎ ከገለጸበት ግዜ ጀምሮ ፍርሃት አገርሽቶ ማህበረሰቡን ሲቆጣጠር ታይቷል።

ታዛቢዎች በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱን በታላቅ አድናቆት ገልጸው የተከሰቱት ጥቃቅን ችግሮች ግን አጠቃላይ ውጤቱን አይለውጥም ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን ባለው ውጤት መሰረት በስልጣን ላይ ያሉት ኡሁሩ ኬኒያታ ለሁለተኛ ግዜ መመረጠቻውን ሲገልጽ ይህም ከደቂቃዎች በኋላ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል።

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/34053