በ24 ሰአት ውስጥ ከ300 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ከባህር መጣላቸው ተሰማ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ ባህር ተሻግረው የመን ለመግባት በጀልባ ይጓዙ የነበሩ ከ300 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በህገ-ወጥ አጓጓዦቹ ተገፍትረው ከባህር መጣላቸውን በህይወት የተረፉት መናገራቸውን የአለም ስደተኞች ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡

የአለም ስደተኞች መ/ቤት  ዛሬ ኦገስት 10 180 ኢትዮጰያውያን ስደተኞችን ጭኖ ወደ የመን ይጓዝ የነበረ ጀልባ ሻብዋ የተባለ አካባቢ ሲደርስ አጓጓዦቹ ስደተኞቹን ሆን ብለው ከባህር የጨመሯቸው መሆኑንና ከእነዚህ ወደ ባሀር ተገፍትረው ከተከተቱት ስደተኞች ውስጥም እስክሁን የ19ኙ አስከሬን የተገኘ መሆኑንና በህይወት ከተገኙት ውጭ ቀሪዎቹን ለማግኘት ፍለጋው እንደቀጠለ መሆኑንና በትናንትናው እለት በአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ጥቂት ሶማሊያውያን የሆኑ ከ120 በላይ ስደተኞች ከተጫኑበት ጀልባ ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ሆን ተብሎ ወደ ባህር መወርወራቸውንና የ50ዎቹ አስከሬን መገኘቱን አስታውቋል፡፡

የአለም ስደተኞች ጉዳይ ቢሮ እንደገለጸው ባለፈው 24 ሰአት ውስጥ ብቻ ባህር ተሻግሮ በጦርነት ወደ ታመሰችው የመን ለመግባት በጀልባ ይጓዙ የነበሩ ከ300 በላይ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ሆን ተብሎ ወደ ባህር ተገፍትረው የተጣሉ መሆኑንና ከእነዚህ ወደ ባህር ከተወረወሩት ስደተኞች ውስጥም እስካሁን የ69ኙ አስከሬን ከባህር ዳር መገኘቱንና በህይወት የተገኙትም የጀመሩትን የስደት ጉዞ መቀጠላቸው ሲታወቅ እስካሁን ባለው መረጃ 13 ስደተኞች የደረሱበት ያለመታወቁ ታውቋል፡፡

በመጨረሻም ባለፉት 6 ወራት ባህር ተሻግሮ የመን የገቡት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሰዎች 55 ሺህ መድረሱን ጠቁሟል፡፡

 

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/34034