በሀረርና በባቢሌ መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው ተባለ

አባይ ሚዲያ ዜና
አክሊሉ ታደሰ

በሀረር ከተማና በባቢሌ ከተማ መካከል በሚገኝ አካባቢ ከባድ ውጊያ እየተደረገ በመሆኑ ወደ ጅጅጋ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱን ጠቅሶ ዜጎቹ ወደ አካባቢው እንዳይጓዙ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማስጠንቀቁ ታወቀ፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲ ጽ/ቤት ለዜጎቹ ደህንነት ሲል ባወጣው ማስጠንቀቂያ እንዳስታወቀው በተጠቀሰው አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑንና ውጊያ እየተደረገበት ነው ወደ ተባለውም ስፍራ ብዛት ያለው የመከላከያ ሰራዊት እየደረስ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ከሀረር ወደ ጅጅጋ የሚወስደው መንገድ ሙሉ በሙሉ የተዘጋ መሆኑን ለዜጎቹ ደህንነት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁም ታውቋል፡፡

ከሀረር ከተማ ወደ ጅጅጋ በሚወስደው መንገድ ባቢሌ አካባቢ እየተደረገ ነው የተባለው ውጊያ ከማን ጋር እንደሆነ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ውጊያው ከባድና ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገበት ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ የመንግስት ሰራዊት በብዛት ወደ ስፍራው እየደረሰ መሆኑ ግን ተገልጿል፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲ እንደተለመደው ለዜጎቹ ደህንነት ባወጣው መግለጫ የተጠቀሰው ስፍራ ለእንቅስቃሴ አደገኛ በመሆኑ ዜጎቹ ወደ አካባቢው ከመሄድ እንዲታቀቡ አስጠንቅቋል፡፡

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/34031