የተራቆተውን የመንግስትና የኤፈርትን ካዝና ነጋዴው እንዲሞላ ሲፈረድበት-የዝረፍ ዘመቻ

[በወንድወሰን ተክሉ]

ትርምሱ አሁን ከአዲስ አበባም ወጥቶ ወደ ተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ተዛምታል። ምስራቅና ምእራብ ኦሮሚያ በተቃውሞ ጩህት ተሞልተዋል። የአማራው ክልል በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከቤት ለቤት የትጥቅ ማስፈታት ድንገተኛ አሰሳ ጐን ለጐን አሁን ደግሞ ቦርሳውን እና ኪሱን ማራቆቻ የግብር ዱላ ታዞበታል።
የአዲስ አበባው ጩህት ይበረክታል-በተለይ በደረጃ “ሐ” ምድብ ውስጥ ያሉት ነጋዴዎች ጩህት ጎልቶ ይሰማል። አቤቱታቸውን ለማሰማት በየወረዳዎቹ ጽ/ቤት ቢኮለኮሉም አብዛኞቹ በአስቸካይ ግዜ አዋጅ ስር ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በሕግ ተከልክላል በሚል ታግደዋል-ወይም እንዲበተኑ ተደርጋል።
የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ አርፈው መቀመጥ ያቅታቸዋል። የአስቸካይ ግዜ አዋጁ የአስቸካይ ግዜ ችግርን ሊሰማ ይገባል ብለው ነው መሰል የተከለከለውን ሰልፍ ትእዛዝ እየጣሱ ወደ ባለስልጣናቱ ቢሮ መተመም ጀመሩ-ቅሬታችሁን በፎርም እየሞላችሁ አስገቡ ተብለው በየቀቤለውና ወረዳው በቅሬታ አቅራቢ ነጋዴዎች እንዲጥለቀለቅ ተደረገ። የዚህ ሁሉ ትርምስና ጫጫታ ምንጭ የሰሞኑ የተተመነው የቀን ገቢ ተመን እና እሱን ተክትሎ የመጣው የዓመታዊ ግብር ተመን ጥያቄ የነጋዴውን ማህበረሰብ እያንጫጫ ያለው። እስቲ ይህን አንጫጪውን የግብር ተመን ይዘቱን እና የአንጫጪነቱን ሃይልና መጠን ጠለቅ ብለን በናሙና መልክ የጥቂቶቹን ታሪክ እየመዘዝን ፈታትሸን እንየው።

**የነጋዴውን ማህበረሰብ እያንጫጫ ያለው የግብር ተመን ይዘት-

መስከረም ታደሰ በካስ ሜዳ ኑር መስጊድ አካባቢ ካሉት አነስተኛ የችርቻሮ ሱቆች ውስጥ አንዳ ባለሱቅ ነች። ጠባብ በሆነችው ሱቃ ውስጥ ከዳቦ ጋጋሪዎች በቀን እስከ 300 ዳቦዎችን እንደምትሸጥ ትናገራለች። ከሸጠችው ዳቦ በቀን 45ብር ትርፍ ታገኛለች። መስከረም ከዳቦው ሌላ ደቦ መጠቅለያ ወረቀትና ፌስታል እንደምትሸጥ ተናግራለች። የቀን ገቢ ገማቾች በቀን 2000ሺህ ብር ገቢ እንዳላትና ዓመታዊ ግብር ተመና 26546 ብር መሆኑን ይገልጹላታል በቀን 45ብር ገቢ ላላት መስከረም።

ላለፉት 6 ዓመታት በአመት 1170 ብር ግብር ስርገብር የነበረችዋ ሌላዋ አነስተኛ ችርቻሮ ሱቅ ባለቤት የቀን ገቢዋን 2500 ብር በማድረግ የዓመቱን ገቢ 26000 ብር እንድትከፍል የተጠየቀች ሲሆን የእሳ የቀን ገቢ ግን 100ብር እንደሆነ በሱቆቻ ውስጥ ያሉትን አስር ሺህ ብር የማይሞሉ ሸቀጣሸቀጦችን ለቪ.ኦ.ኤ እስክንድር ፍሬው እያሳየች ተናግራለች። በ200ብር ካፒታል የጀመርኩትን ሱቅ በቀን ለ100ብር ገቢ የተገመተብኝ 2 እና 3 እጥፍ ሆኖ ቢሆን ኖሮ በደስታ በገበርኩ ግን ይሄ ምን ያህል እጥፍ እንደጨመሩብን እንግዲህ ተመልከት” ስትል ትናገራለች።
ቤቴን ዘግቼ ወደ ልመና መሄዴ ነው የሚሉት ሌላው ከዓረብ ሀገር ተመልሰው ሱቅ የከፈቱትና ተ26000 ዓመታዊ ግብር ፍርደኛ ናቸው።

ያን ያህል ገንዘብ ዓይተነውም አናውቅ በዚህ የችርቻሮ ስራ ላይ ይላሉ። የት ሄደን እንኑር እኛስ ኢትዮጵያዊያን አይደለንም ሲሉም በምሬት በእንባ ይናገራሉ።
ነጋዴው ህብረተሰብ በሶስት የንግድ ደረጃ ተከፍላል። ምድብ “ሀ” ምድብ “ለ” እና ምድብ “ሐ” በሚል። ትልቁ እሮሮና ጩህት እየተሰማ ያለው በምድብ “ሐ” ከተመደቡት የአነስተኛና ዝቅተኛ ነጋዴዎች ክፍል ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ከ300ሺህ በላይ በምድብ “ሐ” የተመደቡ ዝቅተኛ ነጋዴዎች እንዳሉ ይታወቃል። የእነዚህን ነጋዴዎችን ጩህት መንግስት ባቃቃምኩት ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እመረምራለሁ ቢልም አቅምን ያላገናዘበ ተመን ነው የተተመነው ስለሚባለው ወቀሳ ባለስልጣኑ “መንግስት ገማቾችን አስልጥኖ አስተምሮና በተለያየ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ታግዞ የተሰራ ነው” ሲል ይናገራል።

መንግስት አግባብ ያለውን ስራ ነው የሰራሁት በማለት የጫጫታውን መሰረተ ቢስነት ይገልጻል። በሰለጠኑ ገማቾች ነው ግምቱ የተሰበሰበው ቢልም የ300ሺህ ዝቅተኛ ነጋዴዎችን የእለት ገቢ ተመን የሰበሰበው በ30ቀናት ውስጥ ብቻ የመሆኑ ዜና ስራው የግብር ይውጣ አስራር እንዳለው ያሳየናል።

የኢህአዴግ መንግስት ከባለፈው ዓመት ሀገር አቀፍ ዓመጽ በሃል በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው ሰላምና ጸጥታ አልባ ሁኔታ ካዝናው ክፉኛ እንደተራቆተ ተደጋግሞ እንደተራቆተ ተነግራል። በተለይም የውጭ ምንዛሪ አቅሙ አሽቆልቁሎ መንግስታዊ ስራዎቹን እስከማስረዝ አድርሶታል። በ2010 በጀት ከ56ቢሊዮን ብር በላይ ጉድለት እንዳለው ተግልጻል። ነገዴውን ህብረተሰብ ክፍል ይህንን ክፍተት እንዲሞላ የተፈረደበት ይመስላል። አበዳራ ሀገራት በመንግስት የሰብዓዊ መብት አያያዝ አመለካከታቸውን በመለወጥ ቃል የገቡለትን በእጥልጥል ያቆሙ በዝተዋል። በተጨመሪም መንግስት የተራቆተውን ካዝና ለመሙላት ነጋዴውን ሲመርጥ በቀጥታ የሚመለከተው ነዋሪውን ህዝብ ኪስ ነውና ህዝቡ እረፍት እንዲያገኝ እንዳልተፈለገ ግልጽ ነው።

የቁጥባ ቤቶችን ዋጋ በ56% መጨመሩን ይፋ አድርጋል- እያንዳንዱን የህብረተሰብ ክፍል በር በአስጨናቂ የኑሮ ሸክም ትከሻቸውን አጉብጦ አገዛዙን በተደላደለ መንገድ ለመቀጠል ከማለም የመነጨ ቆንጣጭ እርምጃ እንደሆነ ይታያል።

በአስጨናቂ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ያለ ማህበረሰብ ለጨቃኞች ምቹ ተገዢ ይሆናል ሲሉ አምባገነኖች ያምናሉ። የመብት ገፈፋ እና የኢኮኖሚ እድገት መሳ ለመሳ አይጋዙም ብለው ያምናሉ። እናም መብቱ የተገደበበት ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ የደረጀና የጠነከረ እንዲሆን አይፈልጉም። ለአገዛዝ አይመችም ባይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ነጋዴ፣ሸማቹ እና ሰራተኛው ክፍል በአንገት አስደፍቶ ተገዢ በሚያስደርግ ኢኮኖሚያዊ ጥቃት ስር እንዳለ እያየን ነው።

ጉዳዩን እና የግፍ እና የእብሪት አገዛዙን በዝምታ ልናየው አይገባም። ለኢኮኖሚያዊ ተጽእኖም ተንበርካኪ መሆን አይገባም።

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/32334