የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የመብት ረገጣ እንዲጣራ በድጋሚ ጠየቀ

አባይ ሚዲያ ዜና
በአሰግድ ታመነ

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የመብት ረገጣ እንዲጣራ በድጋሚ ጠየቀ።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላቱ “በኢትዮጵያ መንግስት” ላይ የወሰዱት አቋም ለህብረቱ የውጭ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽን ተወካይ ለሆኑት ፌድሪካ ሞግሄርኒ በደብዳቤ እንደደረሳቸው ታውቋል፡፡ ቁጥራቸው 38 የሆኑ የአውሮፓ ህብረት ፖርላማ አባላት በጋራ ለህብረቱ በጋራ ያስገቡት ደብዳቤ “በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚዘረዝርና አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ነው።

እ.ኤ.አ 2016 በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች በተደረጉት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ወቅት የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ግድያ እስራትና የወሲብ ጥቃት ስለማድረሳቸው በደብዳቤው ተዘርዝሯል። በፖለቲከኞችና ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይም ያለ ምንም ህጋዊ መሰረት እስራት እንደተፈጸመና መቀጠሉንም ጠቅሷል። ለአብነትም ከሶስት አመት በፊት ከየመን ታፍነው ተወስደው በኢትዮጵያ እስር ቤት እየማቀቁ ያሉትን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ዋና ፀሀፊ የነበሩትን አቶ አዳርጋቸው ፅጌን ደብዳቤው ይጠቅሳል። የፓርላማ አባላቱ ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ የተከሰተውን ህዛባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች የተወሰዱ እርምጃዎች በገለልተኛ አካላት እንዲጣራና ጥፋተኛ የሆነው አካል ተጠያቂ እንዲደረግ ህብረቱ ድጋፍና ግፊት እንዲያደርግ በጋራ ጠይቀዋል።

ዘገባውን ያወጣው ያልተወከሉ ሀገራት ህዝቦች ተቋም (UNREPRESENTED NATIONS AND PEOPLES ORGANIZATION) የተባለ አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፤ 38ቱን የፓርላማ አባላት የወሰዱትን አቋም አድንቆ፤ እንዲህ ያለው እርምጃ በኦሮሚያ፣ ኦጋዴንና አማራ ክልሎች በተቃዋሚዎችና በሰብአዊ መብት ጠባቂዎች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ለመከታተል ህብረቱ ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብሏል።

የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ የገንዘብ ፈሰስ ከሚያደርግላቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በዜጎች ላይ በሚፈጽመው ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ምክንያት የሚሰጠውን እርዳታ መቀነስ እንዲሁም በተደጋጋሚ መግለጫዎችንና የመፍትሔ ሀሳቦችን ሲያወጣ መቆየቱ ይታወቃል።

 

 

 

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/32331