ስለ ሁሉም ኢትዮጵያውያን “ልዩ ጥቅምስ” ? አከሊሉ ወንድአፈረው

 ሐምሌ 9፣2009

ሕዝቡ ምን ይላል?

የሕወሀት/ ኢህአዴግ  መንግስት ሚኒስተሮች ምክር ቤት ባለፈው ሁለት ሳምንት “ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ስለሚኖራት ልዮ ጥቅም” መጠበቅ በሚል ኣጀንዳ ዙሪያ ለወራት ሲጠበቅ የነበረውን ፖሊሲ (ረቂቅ ህግ) ይፋ አድርጓል።  

የተባለው ፖሊሲ ከያቅጣጫው ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ማጣጣልና ውግዘት ደርሶበታል።  እጅግ ብዙ   የሀገራችን ፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሊሂቃንና የፖለቲካ ተንታኞች ተራ በተራ “ባዶ፣ ውድቅ፣ ከፋፋይ፣ አጥፊ, ዋጋቢስ “ ወዘተ ሲሉ ተችተውታል።

ከነዚህም ወስጥ ለናሙና የሚከተሉትን ማየት ይቻላል።

  • የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ፡)  10 ድርጅቶችን ያቀፈውና የኢትዮጵያ የአንድነት ሀይሎች ትልቁ ስብሰብ የሆነው ሸንጎ በአዲስ አበባ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ለማስጠበቅ በማለት ስርአቱ የወሰደውን እርምጃ “ከፋፋይና በ የተንኮል ሴራ የተሞላ ስለሆነ አንቀበለውም”  በማለት ነው እንዳለ ቦታ ያሳጣው። http://www.ethioshengo.org/files/pressrelease/2017a/Shengo’s%20statement%20on%20Addis%20Abeba%20July%203-17.pdf
  • ሰማያዊ ፓርቲ።ይህ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተረቀቀ የተባለው አዋጅ በጥድፊያ የወጣ፣ግልፅነት የጎደለው፣ህገ መንግስቱን የጣሰ፣በመረጃና በጥናት ላይ ያልተመረኮዘ፣አጠቃላይ የዴሞክራሲ መርሆና ከህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 አላማ ጋር በእጅጉ የተቃረነና ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት አገዛዙ የተነሳበትን የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድ በማሰብ የተቀነባበረ ግልብ ሴራ ፤ ሲል ነው የገለጰው፡  http://www.satenaw.com/amharic/archives/35031
  • ኢደፓ፡  በሊቀመንበሩ በ ዶ/ር ጫኔ ከበደ  በኩል “እያንዳንዱ ዜጋ የሚፈልገው፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ልዩ ጥቅም የሚባል ሳይሆን፤ አገራዊ ጥቅም እንዲኖር ነው።” በማለት ፖሊሲው  አጣጥሎታል-  http://www.sbs.com.au/yourlanguage/amharic/en/content/interview-dr-chane-kebede-0
  • የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)  ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ “የኦሮሞ ህዝብ ልዮ ጥቅም አልጠየቀም ሊጠይቅን አይገባውም፡ በአንድ አገር ሁለት ጥቅም የለም። የተባለው አዋጅ . ምንም የመብት ነገር የለበትም ባዶ ነው” ሲል  ገልጦታል፡ ሌንጮ ባቲ (ቪኦኤ ጁላይ 5፣ 2017)
  • ኦነግ፡ በቃል አቀባዩ በአቶ ቶሌራ አዳባ፡  በኩል “የኦሮሞ ህዝብ  ጥያቄ ለማቀዝቀዝና ለማፈን የተወጠነ ነው” ሲል ዋጋ አሳጥቶታል  (ቪኦኤ ጁላይ 5፣ 2017)
  • የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ የሆነው ጃዋር መሀመድ፡ “ሕወሀቶች እኛን አርስ በርስ አባልተው ሊገነጠሉ ነው   በማለት ነው  የተባለውን የህግ ረቂቅ ማንንም የማይጠቅም አጥፊ ነው ሲል አስምሮበታል http://www.zehabesha.com/amharic/?p=78059

ስርአቱ ይፋ ባደረገው በዚህ ረቂቅ ህግ ላይ ከሚቀርበው ተቃውሞና ነቀፋ ውስጥ በጣም ግልጥ ሆኖ የሚታው ያሁኑ እርምጃ የህዝብ ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት  ከልብ የመነጨና እውነተኛነት ያለው (አውተንቲክ) ሳይሆን የማታለያ፣ የመከፋፈያና ሕወሀት/ኢህአዴግ ከገባበት ቀውስ ለመውጣትና ስልጣኑን ለማጠናከር ያመቻቸው ሴራ ነው የሚለው ነው። ከላይ የገለጥኩት እጅግ ሰፊ ማህበረሰብ ክፍልን የሚወክለው አስተያየት በግልጵ እንደሚያሳየው ፤ የተባለው ረቂቅ አዋጅ በህዝብ አመለካከት ገና ከመወለዱ የሞተ ነው።  ይህ ግን በተወጠነው እቅድ ላይ  ላይ ተጵእኖ ሊኖረው  የሚችለው ህዝብን የሚያዳምጥ የህዝብን ድምጽ የህዝብን ተቃውሞ ቦታ የሚሰጥ  መንግስት ሲኖር ነው። ይህ ባልሆነበት ህግ በህዝብ ላይ በጉልበት የሚጫን እዳ እንጂ ዜጎች ወደው የሚቀበሉትና ባክብሮትም የሚተረጉሙት አይደለም። በመሆኑም ያለፈው ተግባር የወደፊቱን የሚያመለክት እስከሆነ ድረስ ስርአቱ የፈለገውን እያደረገ ህዝብም ብሶቱ እየጨመረ የስርአቱ  ጭነትም ለቅራኔው ተጨማሪ ነዳጅ እየሆነ  ወደ መጨረሻው ምእራፉ ጉዞው ይቀጥላል።

የህዝብ አሰፋፈርና “ልዩ ጥቅም”

አዲሰ አበባና አካባቢዋ የሚተሳሰሩበትን የህግ መሰረት ግልጥ የሚያደርግ  መሰረታዊ ፖሊሲ ማውጣት አንድ ነገር ነው፣፡ ባጠቃላይ በተለያየ ቦታ የሚገኙ ከተሞች (ወይም ትልልቅ ከተሞች) ከክፍለ ሀገረ ወይም ከክልል መንግሰታት ጋር የሚኖራቸውን አጠቃላይ ግንኙነት፣ የሀላፊነት መጠን ህጋዊ ሰውነት፣ ህግ የማውጣት፣ የግብር ህግ የማወጅ፣ በፊደራልና በክልላዊ መንግሰተታት ከከተሞች የሚሰበሰብ ግብር ውስጥ ከተሞች የሚኖራቸው ድርሻ ምን እንደሚመስል የሚወሰን ህግ ማውጣት አንድ ነገር ነው፣። ያንድ ቋንቋ ተጋናሪን (በተለይም በቁጥሩ እጅግ ሰፊ የሆነውን ህዝብ) የተለየ እንክብካቤን  የሚሻ  በማስመሰል በተወሰነ ከተማ ላይ “ልዩ ጥቅም “  እሰጣለሁ ማለት ግን ፣ አንድም በህግ አንጳር ሁሉም ዜጎች እኩል ሳይሆኑ የበላይና የበታች፣ ልጅና የእንጀራ ልጅ በሚመስል  ደረጃ ማሰቀመጥ  ወይም “ልዩ ጥቅምና ልዩ እንክብካቤ”  የሚያሻው ለማን እንደሆነ አለመገንዘብ ነው።

በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ2007 (የዛሬ አስር አመት) በኢትዮጵያ ብሄራዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ በተደረገው የህዝብ ቆጠራ አዲስ አባባ ውስጥ ከሚኖረው ህዝብ ውስጥ በቆጥር በዛ ያሉት አማራ 47%፣ ኦሮሞ   19.5%  ጉራጌ 16.4%  ትግራይ 6% ፣ ሰልጤ 3% ወላይታ .7%፣ ሀድያ .3%  ወዘተ እንደነበሩ ያሳያል ። ከዛ ወዲህ የታየው በወሊድ ወይም የህዝብ ፈለሳ ምክንያት  መጠነኛ ለውጥ ሊኖር ቢችልም ባለው በአጠቃላይ ተዋጵኦው (ፕሮፖርሽን ) ላይ ግን እጅግ የጎላ ለውጥን እንደማያሰከትል መገመት ይቻላል።

መገንዘብ የሚገባው እነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከመሆናቸውም በላይ ብዙወቾ ለስድስትና  ሰባት ትውልድና  ከዚያም በላይ በዚያችው በአዲስ አባባ ተወልደው የኖሩ መሆናቸውን ነው።

በዚህ እውነታ ውስጥ በምትገኝ አዲስ አባባ ያንድ ቋንቋ ተናጋሪ “ልዩ ጥቅም “ አስከብራለሁ ማለት አጅግ ከፍተኛ ፍትህ የጎደለው ብቻ ሳይሆን  በመከባባር በመፈቃቀር፣  በከፍተኛ አንድነት አብሮ በመኖር የሚታወቀውን ህዝብ እጅግ አደገኛ ወደሆነ ክፍፍል እንዲያመራ  በግድ የሚገፋፋ ተግባር ነው። የከተማዋን ነዋሪ  የጋራ ተጠቃሚነትና የጋራ ከተማ ባለቤትንት ስሜት  ሳይሆን አንዱ በሌላው ኪሳራ ተጠቃሚ አስመስሎ የሚያቀርብ፣  በገዛ ሀገሩም ባይተዋርንት እንዲሰማው የሚገፋፋ ተግባር ነው።

አዲስ አበባ በውስጧ የሚኖረው የጉራጌው፤ የከንባታው ፤ የዶርዜው ተወላጅ፣ የኦሮሞው ፣ የጎንደሬው፣ የወላይታው የጎጃሜው፣  የሀረሪው ወሎየው መንዜው የትግራዩ ወዘተ  ነች። የነዋሪዋ ብቻ ሳትሆንም በሀገራችን ዋና ከተማነት የሁሉም ኢትዮጵያዊም ነች።ከተማዋን በሚመለከት የሚወሰድ ፖሊሲም ይህን እውነታ የሚያንጰባርቅ ይህን አብሮነትን እጅግ የሚያጠናክር መሆን ይገባዋል።

ህወሀት/ኢህአዴግ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል ነው ይበል እንጂ ባዲስ አበባ ላይ ያዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ እንደተመለከተው የአዲስ አበባ ነዋሪን የሚመለከተው በባለ ንብረቱ ፈቃድ እንደሚኖር ቤት ተከራይ እንጂ እንደከተማዋ ባለቤት  አይደለም። ቤት ተከራይ ደግሞ መብት ቢኖረውም የመብቱ አይነት ከባለንብረቱ ጋር የማይወዳደር ፣ ዝቅ ያለ ነው። ይህ እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ የሆነ ስርአቱ እስካሁን ሊያርመው ፈቃደኛ ያልሆነ ከፋፋይ አመለካከት ነው።

ቀደምት ሰፋሪነት እና “ልዩ ጥቅም”

አዲስ አበባን በተመለከተ የቀረበው የ“ልዩ ጥቅሙ” ረቂቅ ህግ በከተማዋ ውስጥ ቀድሞ ሰፋሪነትን  መሰረት ያደረገ  ነው ከተባለ ደግሞ አሁን አዲስ አባባ ላይ ተግባራዊ እናደርገዋለን የሚባለው ህግ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችስ ልዩ ጥቅም የሚያሰፈልጋቸው ዜጎች መኖር አለመኖራቸው   መመዘኛው ምንድንው ? ይህ አሁን ባአዲስ አባባ ላይ እንጭነዋለን የሚባለው ህግ በሌሎችስ ከተሞች ወይም የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ተፈጳሚነት ይኖረው ማለት ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።

ለምሳሌ እጅግ ከፍተኛ እድገትን እያሳየች የምትገኘው አዋሳ  እንደ ከተማ ከመመስረቷ በፊት (የዛሬ ስልሳ አመት ገደማ) የሲዳማ ህዝብ ባብዛኛው ለዘመናት የኖረባት ከተማ ነበረች። አሁን ወለጋ የሚባለው አካባቢ የተወሰነ ክፍል በተወሰነ የታሪክ ወቅት  የጎጃም አካል ነበር።  ባንድ ወቅት ድሬዳዋ ባብዛኛው የሶማሊያ ብሄር ተወላጆች ሰፍረውባት እንደነበር ይታወቃል፣  የዛሬዋ ሁመራ ከኢህአዴግ  ወደስልጣን መምጣት በፊት አሁን የሚገኘው የከተማዋ የህዝብ አሰፋፈር አልነበረም የነበራት ፣ ይህ ብቻ አይደለም ባጠቃላይ የወልቃይትና ጠገዴ ጉዳይም ዛሬ ያለውና ከ25 አመት በፊት የነበረው የህዝብ አሰፋፈር አንድ አይደለም ወዘተ ወዘተ። እና ለእያንዳንዱ ቀደምት ቋንቋ ተናጋሪ “ልዩ ጥቅም” የማሰከበር እርምጃ ይወሰዳል ማለት ነው ወይስ ይህ ፖሊሲ አዲሰ አበባ ላይ ብቻ የሚጀመርና የሚያልቅ ህግ ነው? እየተመረጠ ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ ህግ ፍትሀዊነቱ ምኑ ላይ ነው?

በአዲሱ ረቂቅ ህግ አዲሰ አበባን በተመለከተ እንደመነሻ የተወሰደው በአጴ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት   እንደሆነ ተጠቅሷል። መነሳት ያለበት ጥያቄ ለምን፣ ይሀ ጊዜ ተመረጠ የሚለው ነው። ከሚኒሊክ ጊዜ  ወደ  ሓላ ተመልሰን ብንመለከት ደግሞ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የነበረው የህዝብ አሰፋፈር  (አዲስ አበባን ጨምሮ) ምኒሊክ ስልጣን ሲይዙ የነበረውን እንደማይመስል ነው።  በጦርነት፣በተፈጥሮ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ፣ወይም  በተለያየ ምክንያት በተከሰተ ስደት  ወዘተ ህዝብ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሯል። ባንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወይም ቋንቋ ተናጋሪወች በሌሎች ተተክተዋል። በቀድሞው ሸዋም ሆነ በአዲስ አባባና ባካባቢዋም ተመሳሳይ ሁኔታ ተከሰቷል።ይህ ደግሞ አዲስ አባባ በሸዋ ንጉስ ስር ከጅምሩ  ሽዋ በተሰኘው ግዛት ሓላም ራሷን ችላ የኖረችና እንደነበረ በግንዛቤ ውስጥ ማስገባቱ እንዳለ ሆኖ ነው።

ኢትዮጵያ በአለም ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ አንዷ ነች። በርግጥ አሁን ያለው የሀገራችን ቅርጵ አንዳንድ ጊዜ ስትሰፋ ሌላ ጊዜ ስትጠብ ቆይታ በ19ኛውና 20ኛው ክፍለ ዘመን ሀገራችን የያዘችውን ቅርጵ ያንጰባርቃል። ሆኖም ግን የህብረተሰቡን ረጅም ያሰፋፈር ታሪክ፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር ታሪክ፣ የተቆራኘ የመንግሰት ታሪክ ፣ እጅግ ስፋት ያለው ስለመሆኑና ከዚህም ጋር ተያይዞ ያንድ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ  አሁን ባለበት ቦታ ለዘላለም እንዳልቆየ ወዘተ መረጃወቹ እጅግ ብዙ ናቸው።ሰለዚህ የብዙ ሽህ አመታት ታሪክ ያለውን ህዝብ ያለፈው እንዳልነበረ ቆጥሮ  የሚኒሊክን ጊዜ እንደመነሻ መውሰድ ታላቅ ስህተት ላይ ይጥላል።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደሌሎች በኮሎኒያሊስቶች በወረራ የተመሰረተች ሀገር በመቁጠር የሀገር ታሪክን ከኮሎኒያሊስቶች መስፋፋት በፊትና በ ሓላ ብሎ  የታሪክ መስመር  በማሰፈር  ምኒሊክንም እንደወራሪ ኮሎኒያሊስት ከሚፈርጀው የተንጋደደ የታሪክ እይታ ጋር የተዛመደ ነው።

የኮሎኒያሊስቶች የሀገር ምስረታ ታሪክ ጥንታዊ ታሪክ ካላት  ከሀገራችን የህዝብ አሰፋፈርና የአስተዳደር (ግዛቶች)  አመሰራረት  ሂደት ጋር አይጣጣምም። ህብረሰተባችን  ረጅም ታሪካዊ  መሰረት ያለው ህዝብ ነው።  ትልልቅ የሚባሉ የህዝብ አሰፋፈር  ለውጥ ደግሞ በሚኒሊክ ጊዜ፣ በ ግራኝ መሀመድ ( የተለምዶ አጠራር )የመስፋፋት ዘመቻ ጊዜ፣ በታሪክ በታወቀው  የኦሮሞ ፍልሰትና መስፋፋት ዘመን፣ በዛጉየ ክፍለ ዘመን ወዘተ መካሄዱንና ባንድ ወቅት የአካባቢ ነዋሪ የነበሩ የተወሰነ  ቋንቋ ተናጋሪወች በሌሎች አንደተተኩ ወይም የሀያሉን ባህል ቋንቋ ወዘተ እንዲቀበሉና ማናነታቸውን እንዲቀይሩ እንደተደረገ  ታሪክ ያሳያል። ሌላው ቀርቶ ባለፉት 26 አመታት ውስጥ በተካሄደ መንግስታዊ እርምጃ የተለያዩ አካባቢወች የህዝብ ቁጥርና ሰፈራ እንደተቀየረ የሚታወቅ ነው።

የዚህ አይነት የህዝብ ሰፈራ መፈራረቅና መቀያየር በተከሰተበት ህብረተሰብ  የተወሰነ ሀገራችንን አካባቢ ለተወሰነ ቋንቋ ተናጋሪ በባለቤትነት መስጠት እጅግ ብዙ እውነታወችን ያላገናዘበ ይሆናል። አዲሰ አበባም በዚህ እቅፍ ውስጥ የምትታይ ነች።

የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥቅምሰ?

ላለፉት 26 አመታት በተለያየ መልኩ በሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚቀርቡ መሰረታዊ  የመብት መከበር ጥያቄወች አሁንም ምላሸ አጥተው እንዳሉ ናቸው። እነዚህ ጥያቄወች ዛሬ ሊደባበቁ የማይችሉበት ሁኔታ ላይ የደረሱ ከመሆናቸወውም አልፎ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶችም ሊከበሩ የሚገባቸው መሆናቸውን ደግመው ደጋግመው በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚያነሷቸው ሆነዋል። እነዚህ ጉዳዮች የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄወች ብቻ ሳይሆኑ እጅግ የተወሳሰቡት ችግሮቻችንም ለመፍታት ከፍተኛ አሰተዋጵኦ ይኖራቸዋል። ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል።

የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችን መከበር

የስርአቱ መሪወች ስለግል ስልጣንና ምዝበራ  ሳይሆን ስለሀገር ጥቅምና ሰላም የሚያሰቡ ከሆነ ፤ ደጋግሞ እንደሚናገሩት በርግጥም “ጥልቅ ተሀድሶ “ ተደርጎ  ከሆነ፤ ህወሀት/ ኢህአዴግ ለ 26 አመት የሞከረውን ከፋፋይ ፖሊሲ  ወደጎን ወርውሮ የሁሉም  ኢትዮጵያዊ መሰረታዊ መብቶች (ማንነቱን ጨምሮ) የሚከበሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በሩን በመክፈት ህዝባችን የገጠመውን ውስብስብ ችግሮች የሚፈታበት ሁኔታ ማመቻችት ይጠበቅባቸዋል።

ህዝብ የሚፈልገው እርስ በርስ እንዲግባባ፣ እንዲቀራረብ፣ መብቱ እንዲከበር፣ በኢትዮጵያዊነቱም ሆነ ራሱን በሚገልጥበት ማንነቱ እንዲኮራ በድምጱ የመረጠውና ለህዝብ ፍላጎት የሚገዛ  መንግስት እንዲያሰተዳድረው፣ እስራት፣ ግድያ መሬት ነጠቃ ወዘተ እንዲወገድ እንጂ በየወቅቱ የሚከፋፍለውና እርስበርስ የሚያባላው ፖሊሲ የሚፈለፍል ስርአትን አይደለም።

ሕዝብ የሚጠይቀው የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሰረታዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበር እንጂ በከረሚላ እንደሚያታልሉት ህጳን “ይህን አደርግልሀለሁ ያንን እሰጥሀለሁ”  በማለት ለማማለል መሞከርን አይደለም። መብት ማለት ሰወች በሰውነታቸው ወይም በዜግነታቸው ሊያገኙት የሚገባ በህግም የተከበረ እንጂ እንደ ጉርሻ መሪወች ሲፈልጉ የሚሰጡት ሳይፈልጉ ደግሞ የሚከለክሉት ሊሆን አይገባውም። ለዜጎች ክብር መስጠት ከእንደዚህ አይነቱ ተደጋጋሚ አዋራጅ ተግባር መቆጠብንና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የመብት ጥያቄ በተግባር ማክበርን  ይጠይቃል።  ይህ ነው ሁሉንም የሚያረካ የህዝብን ጥቅም የማሰከበር ሀሁ።

በሀገሩ የሚኮራ መሪ የማግኘት መብታችን

እንደማናኛውም ሰብአዊ ፍጡር የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው  በሚገዛት ወይም በሚያሰተዳድራት ሀገር የሚያፍር ሳይሆን የሚኮራ መሪን ነው። ይህ ደግሞ  ባደባባይ ፣ አንገቱን ቀና ድርጎ “ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር”  ብሎ ለመናገር  የማይዳዳ፣ ኢትዮጵያ የሚለውን  ስም ጎላ አድርጎ ለመጥራት የማያፍር ፣ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር የማይተናነቀው መሪ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሁሉንም ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዩጵያዊያንን በሰረታዊ መብት ከማስከበር ጋር አይጳረርም።

የሀገር መሪነትን  “ልዩ ጥቅም “ ከሚፈልግ ድርጅትና ግለሰብ የሚጠበቅ አንዱና ዝቅተኛው ጉዳይ  ከላይ የተጠቀሰው በሀገር መኩራት ነው ። ጆሮ ለራሱ ባዳ ነው እንደሚባለው ካልሆነ የህወሀት/የኢህአዴግ መሪወች ለምንድነው “ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር” ሲሉ ተሰምቶ የማይታውቀው? የኢትዮጵያ መሪወች አይደሉም እንዴ እያለ ህዝብ ደግሞ ደጋግሞ እንደሚያነሳ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ቢያንስ እነዚህን ባህሪወች በተግባርና በግልጥ ማሳየት ነው ህዝብ የናፈቀው።

የኢትዮጵያ የባህር በር መብትና ልዩ ጥቅም

በስልጣን ላይ ያለው ህወሀት/ ኢህአዴግ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራትን  “ልዩ ጥቅም “ በተመለከተ ፖሊሲ ለመንደፍ ውስጥ ውስጡን እየሰራ እንደነበረ በተነገረበት ባለፉት ጥቂት ወራት “ኤርትራን የሚመለከት አዲስ ፖሊሲ ለማዘጋጀት ላይና ታች እያለ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ከዚህ ፖሊሲ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ጥያቄ ለመሆኑ ይህ ስርአት  የሀገር ጥቅምና ታሪክ የሚያንገበግበው ከሆነ፣ ለመሆኑ የኢትዮጵያን ልዩ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ህወሀት ኢህአዴግ የባህር በርን በተመለከተ ምን እያደረገ ነው የሚለው  አንዱ  ነው።

ህወሀት/ ኢህአዴግ በታሪካችን ከሰራቸው ካንድ ሀገሩን የሚወድ መሪ የማይጠበቅ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ውስጥ ሀገራችንን ታሪካዊና ህጋዊ መብቷን ወደጎን አድርጎ የባህር በራችንንና ኢትዮጵአዊ ነን የሚሉ ወገኖቻችንን  ሙሉ በሙሉ ለሽአቢያ ማስረከቡ ነው። ይህ አሳፋሪና አሳዛኝ ተግባር በየትኛውም ሀገር መሪ ያልተደረገ ነው።ልገንጠል የሚሉ ክፍሎችን እንዲገነጠሉ ማድረግ እንድ ነገር ነው፣ በዚህ ሂደት ውስጥ የሀገርንና የዜጎቹን  መሰረታዊ ጥቅም ደግሞ ደጋግሞ አሳልፎ መስጠት ፣ የሀገርን ጥቅም የሚያሰጠብቅ እርምጃ አለመውሰድ ግን እጅግ የተለየ ጉዳይ ነው።

አሁን ያለው ጥያቄም ሕወሀት ኢህአዴግ  ያልበላውን ማከክ ትቶ  በፈጠረው ምስቅልቅል ላይ ሌላ ውስብስብ ችግር ፈጣሪ ተግባርን ትቶ የሀገርንና የሁሉንም ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ወደሚያሰችል አቅጣጫ መቸ ነው ፊቱን የሚመልሰው የሚለው ነው።

ከዚህ ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ በባህር በር ላይ ያላትን ታሪካዊና ህጋዊ መብት “ልዩ ጥቅም “ የሚከበርበትን ፖሊሲ ያዘጋጃል? እውን ለማድረግስ  ተጨባጭ እርምጃ ይወስዳል ? ወይስ ባንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስቴር መለሰ  “  በአሰብ ወደብ   ባለመጠቀማችን  የተጎዱት ኤርትራውያን እንጂ እኛ አይደለንም “http://www.ethioembassy.org.uk/articles/briefings/briefings/Press%20Conferences%20and%20Interviews/Interview%20by%20Meles%20Zenawi%20to%20Voice%20of%20America.htm

ብለው በተናገሩት  አላዋቂ ፈሊጥና የሀገርና የወገንን ደህንነትና ጥቅም  ከማሰብ ይልቅ የሌሎችን መጎዳት እንደ ድል የሚቆጥር እጅግ አደገኛ አመለካከት  ተተብትቦ ቀጣይ ስህተት ውስጥ እንደተዘፈቀና ሀገራችንንም ለአደጋ እንደዳረገ ይኖራል የሚለው ነው።

ይህ በራሰ ሀገር ላይ የተደረገ እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ ታሪካዊ ስህተት ዛሬም ነገም እስከሚታረም ድረስ በቀጣይነት ከትውልድ ወደትውልድ የሚተላለፍ ጥሪ እንደሚሆን ለደቂቃ መጠራጠር ራሰን ማታለል ነው።

ሀላፊነት ከሚሰማው መንግስት የሚጠበቀው የዚህ አይንቱን ቁልፍ ጥያቄ ለመፍታት መጣር የሀገርን ልዩ ጥቅም ለማስከበር የሚቻልበትን መንገድ ተጋባራዊ ማድረግ ፣ ትላንት የተሰራ ስህተትን ማረም የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ወዘተ ነው።

ማጠቃለያ፡

የሕወሀት/ኢህአዴግ መሪወች ለብቻቸው በሚቆጣጠሩት የመንግሰት ስልጣን ከጊዜ ወደ ጊዜ ረጅም እይታ የሚጎድላቸው እርምጃወችን  እየወሰዱ ሲውል ሲያድር የሚከሰተው ውጤትም እጅግ አጥፊ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለህዝብም አብሮነት (  ለራሳቸው ለስርአቱ ደጋፊወችና መሪወች ሳይቀር) እጅግ አጥፊ የሆነ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል።

ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያን ያለ ባህር በር እንድትቀር የወሰዱት እርምጃ፣ በብሄር ብሄረሰቦች መብት ሰበብ ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርገውን አሴት  በማዳከም ወደውስጥ መመልከትን ሚዛን ባጣ ደረጃ እጅግ ገፍቶ የሚሄድበትን ሁኔታወች በፖሊሲም በተግባርም ደረጃ እንዲመቻቹ ማድረጋቸው ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ ናቸው። እንዚህ እውነታወች  ዘግይቶም ቢሆን በስርአቱ ደጋፊወች ጭምር ግንዛቤ እየተወሰደባቸው የሚገኙ ብቻ ሳይሆኑ የስርአቱ መሪወች ራሳቸው ከጊዜ ወደጊዜ በግልጥ ያመኗቸው ሀቆች ናቸው።

እጅግ  የሚያሳዝነው ግን የስርአቱ ፖሊሲ አውጭወች አሁንም ቢሆን ካለፈው ስህተቶቻቸው ሊማሩ አለማቻላቸውና ይበልጥ መከፋፈልን ይበልጥ እርስ በርስ በጥርጣሬና በ”እኛና እነሱ “ ያመለከካከት ካምፕ አክርሮ መጓዝ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ሲያመቻቹ መታየታቸው ነው። ይህ አሳዛኝ ተግባር ሀገራችንን ወደቀጣይ የአደጋ ምእራፍ እየገፋፋት ይገኛል።

ሀገራችን እየተገፋች የምትገኝበት አቅጣጫ ሊያሰከትል የሚችልውን ቀውስ  ቢቻል ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ባይቻል ደግሞ ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት በማለት  ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ሊጨነቅበት እና ሊጠበብበት የሚገባው ፣ በቅንነትም ሊመካከርበትና መፍትሄ ሊፈልግለት  የሚገባ አጣዳፊ ጉዳይ ነው። አደጋው በአብዛኛው በስርአቱ የተፈጠረ ቢሆንም እዳው ግን የሁላችንም ሆኗል።

የኦሮምኛም  ሆነ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ በመሰረቱ የሚፈልገው እንደ ማንኛውም ዜጋ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ (የግልም የቡድንም)  ሳይሽራረፍ ተግባራዊ መሆንን  ፣ በህግ ፊት እኩል መታየትን እንጂ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ልዩ ጥቅምን የተለየ መብትን  ወይም ደግሞ በወረቀት ላይ የሰፈረና በተግባር የማይገለጥ መብትን አይደለም።  

ይህ የተፈጥሮ መብቱ ደግሞ  ከማንም  በችሮታ እንዲሰጠው የሚጠብቀው ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ  በትግሉ የሚጎናጰፈው ነው።  በዚህ ጽሁፍ ላይ አስተያየት ቢኖርወት በዚህ አድራሻ ይላኩ [email protected]

Share Button