ከመላው አውሮፓ ማኅበረ ምመናን የተላለፈ ቤተ ክርስቲያናችን እናድን ጥሪ

ከመላ አውሮፓ ምእመናን የተላለፈ መግለጫ

ሐምሌ 5 ቀን: 2009 ዓ /ም (12. 07 .2017)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ ቤት
አሜሪካ

ጉዳዩ፦ በተወዳጁና በእውነተኛው ሐዋርያዊ አባታችን በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ስም አባ ኤልያስና ቡድኖቻቸው በሚዲያ የበተኑትን የሐሰት ስም ማጥፋት ደብዳቤ የተመለከተ ይሆናል።

በቅርቡ በህዝብ መገናኛ ስላወጣችሁት መግለጫ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ሰኔ 28 ቀን 2017 በቁጥር 27 06 2017 ዝቅ ባለ መልኩ በተጻፈ መግለጫ መሰል ደብዳቤ ስለ ተወዳጁ አባታችን ብፁዕ አቡነ መቃሪዮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የኩቤክ ካናዳና የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ የአውሮፓ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች እያበረከቱት ስላለው አባታዊና ሐዋሪያዊ ተልዕኮ በሰውና በፈጣሪ ዘንድ የሚወደድ ከመሆኑ በስተቀር እውነተኛውን ለመንጋው ዘብ የሚቆሙትን አባታችን በምንም መልኩ አንዳች የሚያስወቅስ ቀርቶ የሚያስተች ነገር እንደ ሌለ እያከናወኑት የሚገኘው የተበተነውን መንጋ የማሰባሰብ አባታዊ ሥራቸው ሕያው ምሥክር ነው።

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ነገር አባ ኤልያስ ለግል ጥቅማቸውና ለራሳቸው ካዘጋጇቸው ቡድኖቻቸው ጋር በመተባበር በታላቋ ቤተ ክርስቲያናችንና በእውነተኞቹ ልጆቿ ካህናትና ምእመናን ላይ እያደረሱት ያለውን መጠነ ሰፊ ጉዳት በተመለከተ ለሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በአውሮፓ ዙሪያ በሚገኙ ልዩ ልዩ ከተማዎች ከየአቅጣጫው አቤቱታ እየቀረበለት ምንም መፍትሔ ሳይሰጥ በዝምታ መቀመጡ እያስገረመንና እያሳዘነን መሆኑ ሳያንስ በበቀለኛውና በቂመኛው በአባ ኤልያስ ጭካኔ የሚባረሩትንና የሚበተኑትን ካህናትና ምእመናን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የአባት ያለሽ በማለት የሚያለቅሱትንና የሚያዝኑትን ሁሉ ከያሉበት ፈጥነው በመሄድና በመድረስ እያጽናኑ እያሰባሰቡ የሚገኙትን ታላቅና እውነተኛ አባት ብፁዕ አቡነ መቃርዮስን ማመስገን ሲገባ በታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን የሥልጣን ማዕረግ ስም በቅዱስ ሲኖዶስ ሰበብ የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሔድ የማይታመን ነውና ከመንጋው ጠላት ከአባ ኤልያስና ከግብረ አበሮቻቸው በስተቀር በትክክል ይህን አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ ያደርገዋል ብለን አናምንም።

የጽሁፉ ይዘት እጅግ የሚያሳዝን ቢሆንም ትናንት ሲኖዶሳችንን በታላቅና ከፍተኛ አባታዊ ማዕረግ ሐዋሪያዊ ተግባራቸውን በሚያውቁ ብፁዓን አባቶች ሲመራ የነበረ ሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ አሁን ግን እኒህ ብፁዓን አባቶች በዕድሜ ባለጸጋነትም ሆነ በተለያየ ህመም ምክንያት የአልጋ ቁራኛ ሆነው ተፈላጊውን ሐዋሪያዊ ተግባር ማከናወን ባለመቻላቸው በረዳትነት መልክ አገልግሎት እንዲሰጡ የተሰየሙት አባቶች እንደነ አባ ሚካኤልና መሰሎቻቸው የተሰጣቸውን ታላቅ ኃላፊነትና አደራ በቅጡ መወጣት ቀርቶ በተሳሳተ አሠራራቸው ሐዋሪያዊና አባታዊ ተልዕኮአቸውን ዘንግተው በዘር በጎሳ በአጠቃላይም ለቅዱስ ሲኖዶሳችን በማይጠቅም መልኩ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ የቡድነኝነትን ስሜት እያራገቡ መታየታቸው በመላው ዓለም የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን እምነት ተከታይ ካህናትና ምዕመናንን በእጅጉ አሳዝኖአል::

በመሆኑም በመግለጫ መልክ የወጣው የመልዕክት ይዘት ለብዙኃን አማኞች አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ቢገኝም ይህ የቅዱስ ሲኖዶሳችንን ጽ/ቤት አስተዳዳራዊ የቀኖና ደምብና ሥርዓት ሳይጠብቅ በጓሮ በር ተጽፎ የተበተነው ጽሑፍ ታላቅ ትዝብትን ቢያተርፍም አሁን በምንገኝበት የመናፍቃንና የተሀድሶ እምነት አራማጆችና ሌሎችም አፍራሽ ሁኔታዎች ያሏቸው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ኃይሎች ተጠናክረው እየተንቀሳቀሱ ባሉበት እጅግ አሳሳቢ ወቅት እነ አባ ሚካኤልና አባ ኤልያስ ከነተከታዮቻቸው በአንጻሩ የሚያካሂዱትን አፍራሽና በታኝ እንቅስቃሴ በብፁዓን አባቶችም ሆነ ሁኔታው ይመለከተኛል ያገባኛል ለሚሉ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ካህናትና ምእመናን ሁሉ በግልፅ የማይታወቅና ያልተብራራ ሁኔታ ባይኖርም ከወዲሁ ከፍተኛ ጥንቃቄና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሃይማኖታችን ክብር ከወዲሁ መነሣት እንዳለብን አጥብቀን እናሳስባለን ::

ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ ከተበተንበት አሰባስበው የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ባርከው በመክፈት በሃይማኖታችንም በጽናት እንድንቆም አስተማሩን ፍቅር ሰጡን እንጂ እንደ ሌሎቹ አባ ኤልያስና አባ ሚካኤል የመሳሰሉት አባቶች ዘረኝነትን ስድብን መለያየትን ተራና ርካሽ ሁኔታዎችን ሲያራምዱ አላየንም፤ አልሰማንም።

አንድ አባት የተሰጠውን ሐዋሪያዊ ሥልጣንና መንጋን የመጠበቅ ሀላፊነትና ተልዕኮ በተጠራበት ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሁሉም ደራሽ የሆነን አባት ማውገዝና መከልከል በሰው የግዛት ክልል አትሂድ፤ አትድረስ በማለት የምታስተላልፉት መልዕክት ወያኔአዊ ሥነ ምግባርን ያካተተ ከመምሰሉም በላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምዕመናንን ወደ ሌላ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሄዱ የሚያደርግ እንጂ ሌላ ፋይዳ እንደማይኖረው በአሁኑ ሰዓት እየተከናወነ ያለው መንጋን የመበተን እኩይ ተግባር ማረጋገጫ ነው። በአንጻሩም ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመረጣቸው ደቀመዛሙርቱ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” ያለውን የማይሻር ቃሉን እየሸረሸራችሁትና እያጠፋችሁት መሆኑን በዚህ አጋጣሚ አበክረን ለመግለጽ እንወዳለን:: እንግዲህ ይህ ሁሉ ሁኔታ ባለበት መልኩ ብፁዕ አባታችን አቡነ መቃርዮስ ባለንበት በአውሮፓና በዓልም ዙሪያ በሚገኙ አህጉራት የአየሩ ጠባይ ማለትም ብርዱና ሙቀቱ ሌሎችም ችግሮች ሳይበግሯቸው ሰብሳቢ እውነተኛ አባት ያጡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ካህናትና ምእመናን ድረሱልን እያሉ ጥሪ ባደረጉላቸው ሀገር ሁሉ እየደረሱ የተበታተነውን አስታዋሽ ያጣውን የተጣላውን ቤት ዘግቶ የተቀመጠውን የታመመውን በየሆስፒታሉ እየዞሩ ቡራኬያቸውን አባታዊ ፍቅራቸውን በመለገሥ ሐዋሪያዊ ተልዕኮአቸውንና አባታዊ ሥራቸውን እያከናውኑ ስለሆነ በእርሳቸው ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ስም አባ ኤልያስና ግብረ አበሮቻቸው የሚያናፍሱትን የስም ማጥፋት ዘመቻ ፈጽመን እንቃወማለን፤ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንም ውጭ ስለሆነ ድርጊቱን ፈጽመን እናወግዛለን።

በአንጻራዊ መልኩ ሲታይ ደግሞ እንደ አባ ኤልያስ ያሉና መሰሎቻቸው ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን የዘነጉ የእውነተኞቹን የነቅዱስ አትናቴዎስን፤ የነቅዱስ ቄርሎስንና የነቅዱስ ዲዮስቆሮስን ቆብና ቀሚስ በማጥለቃቸውና በመልበሳቸው ብቻ የአባትነት ሥም ተሸክመው የአብያተ ክርስትያናትን አገልጋይ አባቶች ካህናትን ሲያዋርዱ ሲያባርሩ ሲሰድቡ ሲከፋፍሉና ቤተ ክርስትያንን ሲያዘጉ ዘረኝነት ጥላቻና ቂም ሲያራግቡ ቤተ ክርስትያንን መደባደቢያ መድረክ እስከሚሆን ድረስ የተጓዙ ሲሆኑ በነዚህና መሰል ሁኔታዎች በተፈጠሩ ጉዳዮች በስዊድን ስቶክሆልም ከተማ አባ ኤልያስ እንደ ግል ድርጅታቸው አድርገው የፈለጉትን የሚያኖሩበት ያልፈለጉትን ደግሞ ሰድበው አዋርደው ካህን ምእመን ሳይሉ ሁሉን በፖሊስ እንድሚያባርሩበት በሰፊው የሚነገርለትን የመድኃኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን እንደ ዋና አብነት በመጥቀስ የደብሩ አስተዳዳሪ የነበሩትን መልአከ ሰላም ብሩኬ አዱኛ ካሣን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ለማባረርበተከሰተው የአድማና የሀሰት የውንጀላ ክስ በሚገኙበት ሀገር ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ችሎት በቀረበባቸው ክስ ተረትተው ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሰ ብር ቅጣት ተበይኖባቸው እንደከፈሉ ለማየትና ለመታዘብም በቅተናል::

ይህም በዚህ እንዳለ በቅርቡ በስዊድን ስቶክሆልም ላይ በአባ ኤልያስ ቤተ ክርስትያን እንዳትደርሱ ተብለው የተባረሩ የተበተኑ ቤት ዘግተው የተቀመጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምዕመናን፤ አባቶች ካህናትና ዲያቆናት ለብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ባቀረቡላቸው የድረሱልኝ ጥሪ በቦታው በመገኘት ማኅበረ ምዕመኑን አጽናንተው አስተምረው በስዊድን ስቶክሆልም ከተማ የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልንና በተጨማሪም የቅዱስ ሚካኤልን ሁለት ጽላቶች ባርከው ቤተ ክርስትያን በመክፈታቸው እንደ ነውርና ኃጢአት ተቆጥሮ በቅዱስ ሲኖዶሳችን ሥም የውግዘትና የማስፈራራት ደብዳቤ ያውም በማይገባው በህዝብ መገናኛ በመነዛቱ እያዘንና እያፈርን በአንጻሩ ግን ከስቶክሆልም መካነ ሰላም ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በቀጥታ ስርጭት ይተላለፍ የነበረውን የታላቁን የሃይማኖት አባትና ሐዋርያ የብጹዕ አቡነ መቃርዮስን ሥርዓተ ቅዳሴና የቃለ ምዕዳን ትምህርት በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ ህዝበ ክርስትያን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደተመለከትነውና እንደተከታተልነው ታላቅ አድናቆትም እንዳተረፉ በዘመኑ ቴክኖሎጂ ሳቢያ ለመገንዘብ ሲቻል ለዚህ የተቀደሰ ሐዋሪያዊ ሥራ ምስጋናና ታላቅ ከበሬታ እንደተሰጣቸው ሁሉ ቅዱስ ሲኖዶሳችንም ሊኮራ በተገባው ነበር እንላለን::

ከፍ ብለው የተጠቀሱት ጥቂቶቹ ሲሆኑ አባ ኤልያስና ቡድናቸው የተካኑበትን አፍራሽ ሁኔታ በማን አለብኝነት ቀጥለውበት በአሁኑ ሰዓት “እግዚኦ መሐረነ” በሚያሰኝ መልኩ ከቅዱሳን ሐዋርያትና ከቀደምት ቅዱሳን አበው ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኒቱን በቀኖናና በሥርዓት በሰብሳቢነት እንዲመራ የተሾመው ፓትርያርክ ወይንም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ባለበት ሲኖዶስ ውስጥ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ያለ ቅዱስ ፓትረያርኩ ፈቃድ በድፍረት ራሳቸው ሹዋሚና ሸላሚ ሆነው የራሳቸውን ሰው የጵጵስና ማዕረግ ሊሰጡ መሰል አጫፋሪ አባቶችንም ለይተው በመጥራት ሽርጉድ በጀመሩበት ሁኔታ ዝግጅት በማድረግ ላይ ስላሉ ብዙ ጎልቶ ያልወጣውን ወያኔነታቸውን ይፋ በማውጣት ቅዱስ ሲኖዶሳችን ለመበታተንና ለመከፋፈል እያካሄዱ ያሉትን ድርጊታቸውን በህብረት ሕዝበ ክርስትያኑ እንዲገነዘበውና እንዲያውቀው ከወዲሁ ለማስገንዘብ እንወዳለን ::

በመጨረሻም አባታችን ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በመገኘት የተበተነውን ሕዝበ ክርስትያን ሰብስበው ያዘነውን አጽናንተው አብያተ ክርስቲያናትን ባርከውና ጽላተ ሙሴውን አስገብተው አባቶች ካህናትንና ዲያቆናትን ወደ እናት ቤተክርስቲያናቸው መልሰው የአደራጇቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አብበው ተበራክተው የሚገኙ መሆናቸውን ስንገልጽ በታላቅ አክብሮትና መንፈሳዊ ኩራት ነው::

ለወደፊቱም ቢሆን በችግራችን ሁሉ ደራሽ የሆኑት የክርስቶስ መንጋ ሰብሳቢ ሆነው በተጠሩበት ቦታ ሁሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንደ እውነተኛው የበጎች እረኛ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ በድሆችና በተናቁት በተገፉት መካከል ለማጽናናት የሚገኙትን እውነተኛውን አባታችን ብፁዕ አቡነ መቃርዮስን የሢመተ ጵጵስና ጊዜያቸውንም እንዲያራዝምልን የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔርን እንለምናለን። የእሳቸው አባትነትና ቡራኬያቸው ተስፋችን እጅግ ከፍተኛ ሲሆን ላበረከቱት ሃይማኖታዊና አባታዊ ፍቅር ሁሉ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ፀጋና በረከትን፤ ረጅም ዕድሜና ጤንነትን እንዲያድልልን እንዲሰጥልን እየተመኘን፤ የእናችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ሁሉ ተራዳዒነት አይለያቸው እንላለን::
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር!!!

ከመላው አውሮፓ ማኅበረ ምመናን የተላለፈ ቤተ ክርስቲያናችን እናድን ጥሪ።

ግልባጭ፦
➢ ለሁሉም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች
➢ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ ቤት
ከያላችሁበት

Share Button