ጥበብ ናቂ [በወንድወሰን ተክሉ]

ጥበብ ናቂ
ክብር ነበር የጥበብ ልብስ
በጨዋ ፊት ሰጪ ሞገስ
ጎንደር ላይ ተሻረ ጥንታዊው ውርስ
ይኮነንን ባወጀ በአፈር ንጉስ
በጎንደር የነጋሾች ዘር
ጎንደር የጋሪዮሽ በር
ጎንደር የአገር ማገር
ጥበብ ወድቆ አፈር ሲከብር
ነጋሽ ተጠይፎ ጥበብ
በህያዋን ሲፈርድ እሱ ለብሶ የድንጋይ ጠረብ
ወጣት ተለቀመ ነገን እንዳለመ
አፈር ለባሹ ጨልሞበት ጎንደርን አጨለመ
ሩጫ ይዘው የተናጠል
የተካኑ በነጣጥል
እሱ ሆኖም ከአፈር
ህያዋንን ሲያስገድል በጎንደር
በነጣጥል ለያይቶ ሊጥል
ሆኖም ከመቃብር ጎንደርን ሊነጥል-እሱ ሲጥር
እምቢኝ አለ ጎንደር
ኢትዮጵያዊነትን በማክበር

በጎንደር ተለብሶ ነጭ ልብስ
እሚያስከብር የአባት ውርስ
እንዴት ዘንድሮ ሆነ ደም አፍስስ
በጥበብ ናቂው በሙታኑ መለስ
ስንቱ ወጣት ተለቀመ
የሙት መንፈስ ስላልተሳለመ
እንዴት በጥበብ ልብስ
ህይወት ይጥፋ ለሟች መለስ

አረ-አረ ወዲያ
ህያዋን ለሙታን ሲሆኑ መሰዊያ
እንዴት ወገን ዝም አለ
ህያው ሆኖ ሲታይ እንደሌለ
እንዴት ዋለ
ከወገኑ ገዳይ አብሮ እያለ
ካልሆነ የሌለ እያለ
ወንድሙን ያጣ ከገዳዩ ባልዋለ

ጎንደር ዝም አይልም
ከወንድሙ ገዳይ አያብርም
ጅግንነትን ያስተምራል እንጂ አይማርም
ይታገላል እንጂ እጅ አይሰጥም

[በነሀሴ ወር 2016 በህወሃት አግዓዚ ወታደሮች በጎንደር ከተማ በመለስ እለተ ሞት ነጭ ልብስ ለብሳችኋል ተብለው በግፍ ለተገደሉት የተጻፈ]

Source Article from http://amharic.abbaymedia.com/archives/32302