ለወያኔ እህቶች ወንድሞች፤ምድረ ኢትዮጵያ፤ አፍሪካ

ከበሪሁን አስፋው

ቶሮንቶ፤ ካናዳ

የመሬት ስፋቱን፤ የውቅያኖስ ጥልቀቱን፤ የፀሃይ ሙቀቱን፤ የጨረቃ ድምቀቱን ያህል እንደምን አላችሁ!

በሰማይ ወይ በምድር የሚኖረው ፈጣሪ የልብ ቅንነቱን፤ ማስተዋሉን፤ እርህራሄውን፤ ቸርነቱን፤ ኢሉኝታነቱን ያድላችሁ።

በሰሜን ሀገራችን በትግራይ በርሃ ከነበራችሁበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ጽሁፍ እስከወጣበት ድረስ የምትጽፉትን፤ የምትናገሩትን፤ ፉከራችሁን ጭምር ተከታትያለሁ።

የበርሃ ፉከራችሁን፤ ማለት ኢትዮጵያን በቋንቋ፤ በዘር፤ በሃይማኖት፤ በአካባቢ እንከፋፍላለን፤ አማራ የሚባለውን ነገድ ከምድረ ኢትዮጵያ እናጠፋለን፤ የትግራይን መንግሥት በአማራ መቃብር ላይ እንመሠርታለን እያላችሁ ትናገሩና፤ ትፎክሩ የነበረውን ሁሉ ከፕሮፖጋንዳ ውጭ በሥራ ላይ ታውላላችሁ የሚል እምነት ፈጽሞ አልነበረኝም። አላመንኩም፤ በትልቁ ተሳስቻለሁ።

በምን ምክንያት ለሁለት ሦስት ሽህ ዓመታት አብሮ የኖረ፤ አብሮ የወደቀ፤ አብሮ የተነሳ ሕዝብ የኢትዮጵያ የመሠረት ድንጋይ ከተተከለበት ከጥንታዊት ትግራይ የተወለደና ያደገ ወያኔ ኢትዮጵያን ያጠፋል ብዬ ልመን? የሌሎችን ሀገሮች ታሪክ፤ የፖለቲካና የሶሻል ሂደት፤ በተለይ የተንኮል ምንጯን የእንግሊዝን፤ የታሪካዊ ጠላቶቻችን፤ የግልቡ የኢጣሊያንን፤ እንዲሁም በጥቁር ክፍለ ዓለማችን በጥንታዊው የአፍሪካ ምድር የምትገኘው የደቡብ አፍሪካ የነጮች ታሪክ በተወሰነ ደረጃ ተከታትያለሁ። ከእናንተ ወያኔ እህቶቻችን፤ ወንድሞቻችን መንግሥት ጋር ለማነጻጸር ሞክሪያለሁ። ብትበልጡ እንጅ አታንሱም። እንዲያውም የዓለምን ታሪክ ካመሰቃቀሉት የቅኝ ገዥዎች በልጦ ለመገኘት ትጥራላችሁ። በእርግጥም ትበልጣላችሁ።

በሪሁን አስፋው
በሪሁን አስፋው

ከእናንተ እህⶆቻችንና ወንድሞቻችን ውስጥ የቀድሞቹን የፖለቲካ፤ የዘመናችን የእጅ አዙር ፖለቲካና የምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚ) ቅኝ ገዥዎች፤ በተለይ የተንኮለኛዋን እንግሊዝን፤ የፈረንሳይን፤ የጣሊያንን፤ የደቡብ አፍሪካን የነጮች አገዛዝ፤ አመራር የታሪክ፤ የፖቲካና የህብረተሰባዊነት (ሶሻል) ሂደት የተመራመሩና በዚህ የከፋፍለህ ግዛ ፍልስፍና የተካኑ፤ ከተቀሰፈው ሊቁ ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ የተንኮል ምሁራኖች በውስጣችሁ መኖራቸውን እያየን ነው።

በዚህ ምክንያት እንኮራበታለን እንወክለዋለን ከምትሉት ከሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል  ከትግራይ ጥንታዊ ታሪክ፤ ባህል፤ ሃይማኖትና ሥነ-ጽሁፍ ውጭ ሥልጣኔ መስሏችሁ ይሁን፤ ወይም በየዋህነት “ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ” እንዲሉ የቅኝ ገዥዎችን የከፋፍለህ ግዛ ፍልስፍና፤ የፖለቲካና የምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚ) ሂደት በበለጠ ከሥራ ላይ አውላችኋል። ከእነሱ በልጦ ለመገኘት ያደረጋችሁትና የምታደርጉት ጥረት ከሥራ ላይ ውሏል። የውጮቹ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን እየበዘበዙና እየዘረፉ ወደ አገራቸው ልከው የአገራቸውን ኢኮኖሚ ሲያዳብሩ፤ እናንተ ደግሞ ከድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎሮሮ እየቀማችሁ፤ እየዘረፋችሁ፤ የውጭ ሀገር ባንኮችን  ታዳብራላችሁ። በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ “እምብርት” የለሽ፤ በልቶ የማይጠግብ፤ ሰው ምን ይላል የማይል ኢሉኝታ የሌለው መንግሥት ታይቶ ተሰምቶ አያውቅም። ምናልባትም በአፍሪካ። እናንተንና ከፍ ተብሎ የተጠቀሱትን ቅኝ ገዥዎች እንግሊዝን፡ ፈረንሳይን፡ ጣሊያንን፡ እና ደቡብ አፍሪካን ነጭ ሰፋሪ ቅኝ ገዥዎች የሚለያችሁ እነሱ ከሌላው የዓለም ክፍል የመጡ ነጮች፤ እናንተ ደግሞ አገር በቀል የሆናችሁ ጥቁሮች መሆናችሁ ነው። የተጠቀሱት ወራሪ ቅኝ ገዥዎች ከአውሮፓ ወደ አፍሪካ ሩቅና መካከለኛው ምሥራቅ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ባልተወለደ አንጀታቸው የፈጸሙት ግፍና ዘረፋ፤ እናንተ በገዛ ሀገራችሁ ደሃ ሕዝብ ላይ የምትፈጽሙት በሚዛን ሲቀመጥ የናንተ ይመዝናል ብዬ አምናለሁ። የገባው ተማሪ ባትሆኑም ጥሩ ፎቶኮፒ ገልባጭ ናችሁ።

የእነሱን የከፋፍለህ ግዛ ፍልስፍና የገለበጣችሁና ታማኝ አገልጋዮች በመሆናችሁ በኢትዮጵያ የሥልጣን ኮረቻ ከተቀመጣችሁበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት፡ የፖለቲካና የሞራል ድጋፍ ያደርጉላችኋል። ቅኝ ገዥዎቹ ሞክረው ሞክረው ኢትዮጵያን ያገኟት አሁን ነው። ከ15ኛው (አስራ አምስተኛው) ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተለያይዩ ዘመናት እየተፈራረቁ ቱርክ፤ አሽከሯ ግብጽ፤ እንግሊዝ፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛት አድርገው ለመግዛትና ለመበዝበዝ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይሞክሩ እንጅ፤ በቀጥታ እጃቸውን ሳያስገቡ፤ የሚፈልጉትን የሚፈጽም “ሳይጠሩት አቤት፤ ሳይልኩት ወዴት” የሚል ሎሌ አግኝተው አያውቁም። በዚህ ምክንያት መዕራብ የብር ዝናብ አዝንቦ ጎርፍ ይዟችሁ ሊሄድ ነው።

ምንም እንኳን የተወለድኩበትና ያደኩበት የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት፤ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ጥራዝ ነጠቅ ሶሻሊስት መንግሥት እንተወውና፤ በተባበሩት መንግሥታት የቀዝቃዛው ጦርነት፤ በከበርቴው ካፒታሊስት ምዕራብና በሶሻሊስቱ ምሥራቅ ይካሄድ በነበረው “የፖለቲካ ግብግብ” የአጼው መንግሥት ምእራብን በመደገፍ በተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ድምጽ እጁን ያንሳ እንጅ፤

ምንም እንኳ በንጥቁ ኃያል ሀገር በአሜርካ በተመራው የኮሪያ ጦርነት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1942-1945 ዓ.ም በቻይና በተደገፈው የሰሜን ኮሪያ እና በአሜሪካ በተደገፈው የደቡብ ኮሪያ ጦርነት ኢትዮጵያ የጦርነቱ ተካፋይ እንድትሆን አድርጎ ብዙ ወታደሮች (ክቡር ዘበኛ ጦር) ይሰዋ እንጅ፤

ምንም እኳ የአጼው መንግሥት በቬትናም ጦርነት በተባበሩት መንግሥታት በአሜሪካ በተመራው የመእራብ ቡድንና፤ በቀድሞው ሶቬት ህብረት በተመራው የምሥራቅ ቡድን መካከል በተካሄደው ንትርክና ሙግት ድጋፉን ለመእራቡ ዓለም ይስጥ እንጅ፤

በኮንጎ(በዛዬር) አሜሪካና የኮንጎ ቅኝ ገዥ በነበረችው ቤልጅግ በቆሰቆሱትና ባስነሱት የእርስ በርስ ጦርነት የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት የንጥቁን ኃያል ሀገር የአሜሪካንን ፍላጎት ለመፈጸም የኢትዮጵያን ጦር ሠራዊት ወደ ኮንጎ ይላክ እንጅ፤

“ለወያኔ” የዘነበው የብር ዝናብ አላካፋለትም። ምክንያቱ ግልጽ ይመስለኛል። የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት  ምንም እንኳ የአገሯን ድህነት ቢያውቅም የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና ኩራት፤ ክብር በመጠበቅ “ኩራት እራቴ” ስላለ ይመስለኛል። እንደ ወያኔ አቤት ወዴት ብሎ የአገሯን ጥቅምና ክብር አሳልፎ ቢሰጥ ባይዘንብለትም ያካፋለት ነበር ብዬ አምናለሁ።

የአጼው መንግሥት በ1966 ዓ.ም ሊወድቅ በሚንገዳገድበት ጊዜ እንኳ ምዕራብ የፖለቲካና የሞራል ድጋፍ ነፍጎታል። የምእራቡ ዓለም ኢትዮጵያን የሚጠላበት ምክንያት ከፍ ተብሎ ከተጠቀሰው ሌላ የኢትዮጵያ ነገሥታት አክሱም ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ነጻነት በመጠበቅና በመከላከል ለአፍሪካ ትልቅ የነጻነት ትግል ምልክትና አርአያ ሆና በመገኘቷ ነው ብዬ አምናለሁ። በመላ ዓለም ታሪክ ነጻነቷን ጠብቃ የኖረች ብቸኛ ሀገር መሆኗ በመእራብ አልተዋጠላቸውም፤ ባንዳው ወያኔ የኢትዮጵያን ታሪክና ሀገራዊ ኩራት በጨረታ እስከ አቀረበበት ድረስ። ጽሁፏ ጥንታዊ፤ ከፎኒሻ – ከአሁኗ ሊባኖን ነጮች ከወሰዱት “ላቲን” ጋር የሚወዳደር; የራሷ የቀን፤ የሰዓት፤ የዓመተ ምህረት አቆጣጠር ያላት፤ የክርስትና ሃይማኖት ከሮም ጋር በአንድ አካባቢ የተቀበለች፤ የአሜሪካ ወላጆች እነ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይ፤ ጀርመንና ሌሎች አውሮፓዊያኖች በዋሻ በሚኖሩበት ዘመን ታላቅ ሀገር የነበረች፤ በሰባተኛው መእተ ዓመት አዲሱ የእስልምና ሃይማኖት “በነብዩ መሀመድ ሐዋርያነት ከተጀመረ በኋላ ተከታዮቹ በአዲሱ ሃይማኖት ምክንያት ሲጨፈጨፉ ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ ያስተናገደች ሀገር በመሆኗ፤ በመጽሀፍ ቅዱስ ስሟ 48 ጊዜ የተጥቀሰ፤ ከሁሉ በላይ የሰው ዘር ምንጭ የሆነች፤ አፍሪካዊ ሀገር በመሆኗ “አንዲት ድሃ ሀገር” እንዴት ተብሎ ከኛ በለጠች የሚል ጥላቻ ምዕራብ አብቅሏል ብዬ አምናለሁ። የአሁኑ የዎያኔ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን መንግሥት የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ልማድ፤ ባህል እና አገራዊ ኩራት ክዶ ለዶላር እጅ ነስቶ ስለተንበረከከ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለናንተ የሰጠውን የአንድ ዓመቱን በሰላሳ ሶስት ዓመት መንግሥታቸው ጊዜ አልሰጠም።

ይህን ከዚህ ላይ እንቋጨውና፤ ለመሆኑ፡ ወያኔ እህቶች፤ ወንድሞች የአማራን ጥላቻ የት አገኛችሁት?? አማርኛና ትግረኛ ተናጋሪዎች ከታሪክ እንደሚነበበው፤ በቤተ ክርስቲያን ገድልም ሆነ በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አብሮ የኖረ፤ የተቀልቀለ፤ ሁለንተና ባህሉም ሆነ ልምዱ አንድ የሆነ፤ የሰውነት ተክሉም ሆነ የቆዳ ቀለሙ ከሌሎቹ የብሄር ተወላጆች ጋር በመጋራት አንድ የሆነ፤ የማይለያይ፤ በታሪክ አብሮ የተነሳ፤ አብሮ የወደቀ ሕዝብ ነው። ለምድን ነው አማራን ከምድረ ግጽ እናጠፋለን ብላችሁ ለተከታዮቻችሁና ለልጆቻችሁ ያስተማራችሁ? የጻፋችሁ? እስኪ አንድ፤ ሁለት፤ ሶስት፤ አራት ብላችሁ ያልገባንን ሰዎች አስረዱን!!

በአማርኛና በትግረኛ ቋንቋዎች መለያየት አንድን ሕዝብ ይለያየዋል ማለት አይደለም። ወይም አንድ ቋንቋ መናገር አንድን ሕዝብ አንድ ያደርገዋል ማለት አይደለም። ቋንቋ አንድን ሕዝብ አንድ ያደርገዋል የተባለው እውነታ ቢኖረው ኖሮ ቋንቋውም ሆነ ሃይማኖቱ የመለካ ምድር (ጂአግራፊ) አቀማመጡ አንድ አይነት የሆነው የሶማሌ ሕዝብ ከዚህ እልቂትና ምስቅልቅል ባልደረሰ ነበር። አንድ ቋንቋ አንድ ሃይማኖት፡ አንድ የተመሳሰለና የተያያዘ ታሪክ የተጎናጸፈው የአረቡ ዓለም እርስ በርሱ አይፈነካከትም ነበር። የአረቡ ዓለም የትምህርት (የመጀመሪያዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች የተመሠረቱት ዓረብ ዓለም ነው) የሳይንስ፤ የቁጥር፤ የኢንጅነሪንግ፤ የአርክቲክቸር፤ የሥነ ሥሁፍ፤ የህክምና፤ የፊደል፤ የዕርሻ፤ ወዘተ.. ምንጭ ይሁን እንጅ ይህ ሁሉ ታሪክ እንዳልጠቀመው እያየን ነው።

የአማርኛና የትግረኛ ቋንቋ ልዩነት ከአንድ የቋንቋ ቤተሰብ በመምጣቱ ጥሩ አማርኛ የሚናገር ትግረኛ በመጠኑ ይገባዋል። ትግረኛ ተናጋሪውም እንዲሁ አማርኛው ይገባዋል። ስለዚህ አንድ ቋንቋ መናገር የአንድነት ዘላቂነት ይኖረዋል ብሎ ማመን የዋህነት ይመስለኛል። ወያኔ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ቋንቋን እንደ ትልቅ መለያያ ቆጥራችሁ በመነሳትየሥልጣናችሁ መሠረት አድርጋችሁ ኢትዮጵያን ለክፉ ውድቀት ዳርጋችኋል። የኢትዮጵያን ምድር በቋንቋ፤ በሃይማኖት ከፋፍላችኋል። ይህን ያደረጋችሁት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አስባችሁ ወይም ወዳችኋቸው ሳይሆን ከፍ ተብሎ በሌላ ቦታ እንደተጠቀሰው የቅኝ ገዥዎችን የከፋፍለህ ግዛ ፍልስፍና በመከተል እኛ የበላይ ሆነን እንገዛለን፤ እንበዘብዛለን በማለት ነው። ይህም እስካሁን ድረስ ያየነው ሥራችሁ አሳይቶናል።

የሚገዛውን ሀገር ሕዝብ በሰላም “እንዴት” አብራችሁ ትኖራላችሁ፧ ለምን አትጣሉም፤ የሚል፤ ይህንንም ሳያፍር ከሥራላይ የሚያውል መንግሥት በኢትይዮጵያ ታሪክ ኖሮ አያውቅም፤ ምናልባትም በዓለም ታሪክ። እናንተ ግን ለምን በሰላም ሕዝቡ አብሮ ይኖራል፤ ለምን አይጣላም፧ እያላችሁ በህልማችሁም በውናችሁ በሥራ ላይ አውላችኋል። የሥልጣን ምሰሷችሁ ይህ ክፉ ሥራችሁ ሆኗል። ይህ እናንተ በሥራ ላይ ለማዋል የሞከራችሁት ሃያ አምስት ዓመት በሥልጣን ላይ እንድትቆዩ ይጥቀማችሁ እንጅ ይህን ክፉ ሥራችሁን ሕዝቡ ስለተረዳው ነቅቷል። እየመሸ ነው። ይህን ግድ ተጣሉ፤ “ፖሊሲ” ጣሊያንም ሞክሮ አልተሳካለትም። እናንተ የበለጠ ለማድረግ እንደሞክራችሁት ሁሉ ጣሊያን ሕዝቡን በጎሳ፤ በሃይማኖት፤ በዘር፤ በአካባቢ፤ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በክርስቲያኑ፤ ኦሮሞና፤ ሌላው ጎሳ በአማራ ላይ እንዲነሱ ያልጠረገው መንገድ፤ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። አልተሳካለትም። እናንተም ይህ ጽሁፍ በሚጻፍበት ጊዜ እንደምናየው ሜዳው ገደል ሆኖባችኋል።

“አባ ዶዬ” የተባሉ የሸዋ ኦሮሞ ባላባት የአካባቢው የጣሊያን ገዥ ጠርቶ “ለምን እናንተ በአማራ ላይ አትነሱም” ብሎ ሲጠይቃቸው አንድ ቁና ጤፍ ወስደው በማሳየት ‘እኛ እና አማራ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዚህ ጤፍ የተቀላቀልን ነን’ በማለት ሕዝቡ አብሮ የኖረ የተዋለደ እና የተጋባ መሆኑን የገለጹና ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅነት የጣሊያኑን መኮንን ማስተማራቸውን የሸዋ አዛውንቶች ተናግረዋል።ተጽፏል። አባ ዶዬ የታወቁት የካፒቴን አዳሙ፤ የኮሎኔል ሥምረት መድሃኔ እና የሌሎች አያት ናቸው።

ወያኔዎች አማራ ትግራይን በድህነት እንድንኖር፤ ወደኋላ እንድንቀር አደረገ ትላላችሁ። ለመሆኑ ከዲስ አበባ አፍንጫ ሥር የሚኖረው ብዙዎቹ የሸዋ መኳንቶች የሚወለዱበት “መንዝ” ከአድዋ፤ ከሽሬ፤ ከተንቤን፤ ወዘተ የተሻለ ነው? ሕዝቡ የተሻለ ኖሮ ይኖር ነበር? የጎጃም አቸፈር፤ የጎንደር ወገራ፤የወልቃይት፤ የየጁ ወሎ፤ የላስታ ባላገር ከተንቤን ‘ ከሽሬ፤ ከእንደርታ ባላገር ወይም ገበሬ የተሻለ ንብረት ነበረው፧› የተሻለ ተምሯል? የተሻለ የጤና አገልግሎት አለው? የተሻለ አስተዳደር ነበረው? መልሱን ለእናንተ ትቸዋለሁ።

አሁን በህይወት እስካሉት ለዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ድረስ ሰሜናዊ ሀገራችንን ትግራይን የገዙት እኮ አማሮች አይደሉም። ኦሮሞዎች አይደሉም፤ ጉራጌዎች .. ወዘተ አይደሉም ። የትግራይ ተወላጆች የሆኑት እንጅ። አማራ እንዴት እንዳደኸያችሁ ብትነግሩን፤ ብታስተምሩን ጥሩ ይመስለኛል። እንዲያው በደፈናው ሕዝቡን በውሸት ፕሮፖጋንዳ ለማወናበድ ከመጣር ይልቅ።

አንዳንድ የወያኔ ደጋፊዎች አውቀናል፤ ተራቀናል ባዮች ታሪክን ገልብጠው ያነባሉ። ያልነበረውን ነበር፤ የነበረውን አልነበረም በማለት የትግራይ ግዛት የተከዜን ወንዝ ተሻግሮ እንደማያውቅ ጥንታዊው መጽሃፍት ያስተምራሉ። ጥንታዊ የመልካ ምድር አቀማመጥ ካርታዎች በምድር ያለውን ዕውነታ ያሳያሉ። በጥንት ጊዜ በጎንደር መንግሥት ዘመን ከዚያ በፊት ኢትዮጵያን የጎበኙ የውጭ ሀገር ሰዎች ጽፈዋል።

ጀምስ ብሩስ የተባለው የስኮትላንድ ተወላጅ ከትግራይ ወደ ጎንደር ሲሄድ ተከዜን እንደተሻገረ አማራ ግዛት መግባቱን በሁለት ጥራዝ መጽሃፍቱ ዘርዝሯል። በአጼ ልብነድንግልና በአጼ ሲስኖስ ጊዜ ከዚያም በጎንደር መንግሥት የመጡ የፖርቱጋል ቀሳውስቶች የማራና የትግራይ ወሰን ተከዜ መሆኑን ጽፈዋል። ከቅድመ አያⶆቸው ጅመሮ ለመቶ ዓመታት ያህል ትግራይን ከገዙት የሚወለዱት የመጨረሻው አሁን በህይወት ያሉት ራስ መንገሻ የትግራይና የአማራ ወይም የቤጌምድርና ሰሜን ክልል ተከዜ እንደሆነ ተናግረዋል።

ውሸታሞቹ የወያኔ የታሪክ ሰዎች ራስ መንገሻ የሚሉትን ካለመቀበላቸው ሌላ እሳቸውን በማጥላላት የተለያየ የስም ማጥፋት ዘመቻ ጀምረዋል። ውሸታሞቹ የታሪክ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት አዛውንቱ ራስ መንገሻ ለምን እንደኛ አልዋሹም በማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ከውልቃይት፤ጠገዴ፤ ከጸለምት ሌላ አርማጭሆ፤ ሰሜን ራስ ዳሽን፤ ላስታ፤ ላሊበላ፤ የኛ የነበረ፤ የኛ ነው ይላሉ- የማያፍሩት ወያኔዎች።

የወያኔ የግዛት ማስፋፋት ዋና ምክንያት ሆኖ የቀረበው ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጸለምት ትግርኛ ይናገራል በማለት ሲሆን፤ ግን ደግሞ ደንበኛውን ትግረኛ ተናጋሪ የኤርትራን፤ የሐማሴን፤ የሠራዬን፤ የአካለ ጉዛይን ሕዝብ ነጻ ሆኖ ከትግራይም ሆነ ከኢትዮጵያ እንዲገነጠሉ መስዋዕትነት ከፍሎ ተግባራዊ አድርጓል።

የአማራ ሕዝብ የሆነውን የወልቃይት፤ የጠገዴ፤ የጸለምት ሕዝብ በጠመንጃ አፈሙዝ አማራዎች አይደላችሁም፤ ትግሬዎች  ናችሁ፤ የአፋርንና  የወሎን ግዛቶች የነበሩትን ክልሎች የትግሬ ናችሁ፤ አማራም ፤ አፋርም አይደላችሁም በማለት በውንብድና እና በጥጋብ የተወጠረው ወያኔ በማን አለብኝነት ያቀላቅል እንጅ “ቅልቅሉ” ውሃና ዘይት ስለሆነ ፈጽሞ ሊቀልቀል አልቻለም። አይችልምም።

የወያኔ ልክስክስነት ወልቃይት ጠግዴን፤ ጸለምትን በጠመንጃ አፈሙዝ በተራ ውንብድና፤ በማጭበርበር፤ ከወሰደ በኋላ ጎንደር ሲገባ ጣሊያን የተከለውን ብቸኛውን የኤሌክትሪክ ሞተር ነቅሎ መውሰዱ ነው። ምናልባት ሞተሩ ትግረኛ ተናጋሪ ኖሮ ይሁን?! የሚከላከል ሰው ቢጠፋም ሞተሩ ራሱ እምቢኝ አልነቀልም ብሎ ዘርፊዎቹን አስቸግሮ እንደነበር የጎንደር ሕዝብ መነጋገሪያ ሆኗል።  “ሀገር ያልዘረፈ መንግሥት ምን መንግሥት ነው” ነበር የወያኔ መርሆና ፍልስፍና። ወያኔ ሆድ አምላኩ የሆነ በልቶ የማይጠግብ ሆዳም ድርጅት ነው። የወያኔ መሪዎች አስተሳሰብ ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው የሚለየው በፈረንጅ ልብስና በከራባት ብቻ ነው። የድሮዎቹ ቢዘርፉም ከዘረፉት ሕዝብ ጋር ተካፍለው ይበላሉ። ወያኔ ግን የዘረፈውን ቤቱን ዘግቶ ብቻውን የሚበላ፤ በልቶ የማይጠግብ ፍጥረት ነው። ከቀድሞዎቹ አጼዎች፤ ተዎድሮስ፤ ተክለጊዎርጊስ፤ ዮሐንስ፤ ምኒልክ፤ ዘመኖች አስተሳሰብ በእንግሊዝኛ ከመኮላተፍና ከከራባት በቀር ቢያንስ እንጅ አይበልጡም። የእነሱ አብሮ የመብላትና ሰው ምን ይላል የሚለው፤ “ሰው ባያይ እግዚአብሔር ያያል” የሚለው አስተሳሰብ የሌለው ሆድ አምላኩ የሆነ ድርጅት ነው። ይሁንና ይህን ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይዞ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እራመዳለሁ ይላል። በጠመንጃ አፈሙዝ፤ በተንኮል፤ ሰውን በመግደልና በማሰቃየት በተደገፈ ትምክህት ሲራመድ ወድቆ መሠበሩ አይቀሬ ጉዳይ ነው። ይህም በታምረኛዋ ኢትዮጵያ ሰማይ እየታዬ ነው።

ከወያኔዎችና ከእጋፊዎች ምሁራን ነን ባዮች ምክንያቶች አንዱ የሚነገረውና የሚጻፈው ከአጼ ዮሐንስ የመተማ መስዋዕትነት በኋላ “የኛ የትግሬ መንግሥት በሸዋ በአጼ ምኒልክ ከአጼ ዮሐንስ አልጋ ወራሽ ከራስ መንገሻ ዮሐንስ በጉልበት ተነጥቆ ተወስዶብናል” የሚል ነው።  ወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው ያልገባቸው ወይም እንዲገባቸው የማይፈልጉት ግን ከሚያስቡትም ከሚያምኑበትም ውጭ ነው።

የጉልበት ነገሥታቶች ዘመን የተጀመረው በአጼ ቴዎድሮስ ሲሆን፤ የቀጠሉት ነገሥታቶችና በኋላ የመጡት መሪዎች አጼ ተክለጊወርጊስ፤ አጼ ዮሐንስ፤ አጼ ምኒልክ፤ (እያሱንና ዘውዲቱን ትተን) አጼ ኃይለ ሥላሴ፤ እሳቸውን የተኩት መሪዎች በቅደም ተከተል መንግሥቱ ኅይለማሪያም(ደርግ) ፤ መለስ ዜናዊ ወያኔ ሁሉም ወደ ዙፋንና ሥልጣን የመጡት በጉልበት እንጅ ሲወርድ ሲዋረድ ይመጣ እንደነበረው በውርስ አልነበረም። አይደለም። የቴወድሮስ፤ የተክለ ጊወርጊስ የዮሐንስ የምኒልክ፤ (ሶስት ዓመት ኢያሱ በቀር)፤ የአጼ ኃይለሥላሴ ልጆች አልወረሱም። ያን ጊዜ የነበረው የመውረስ ህግ እንደ ቅድመ አጼ ቴወድሮስ ከአባት ወደ ልጅ ሳይሆን በጎራዴና ጋሻ በጉልበት ስለነበር መንገሻ ዮሐንስ ስለተሸነፉ ተወስዶባቸዋል። ቢያቸንፉ ኑሮ ምኒልክ የሚወስዱበት መንገድ አልነበረም። መንገሻ በጊዜው በነበረው “የጎራዴና የጋሻ” ህግ ስለተሸነፉ ተወስዶባቸዋል። አጼ ዮሀንስ እንኳ የወሰዱት ከአማቻቸው ከአጼ ተክለ ጊወርጊስ በጉልበት በሚዘገንን ሁኔታ እንጅ በውርስ አይደለም። ስለጉልበታሞቹ ነገሥታት አወራረስ ከዚህ ላይ እንተወውና፦

ከገናናው የኢትዮጵያ መንግሥት መሠረት ከአክሱም መንግሥት ውድቀት በኋላ መሠረታቸው ከአክሱም የሆኑ ነገሥታቶች በላስታ፤ በሸዋ፤ በጎንደርና በሌሎች ቦታዎች በመከተም እስከ ፍጻሜ መግሥት ኃይለሥላሴ ድረስ ቀጥለዋል።

የታላቋ የሮማ መንግሥት ኋላ ቀር በነበሩ ጀርመኖች፤ ፈረንሳዮች፤ ስፓኒሾች (ስፔን) ኦርስትሪያዊያኖችና ሌሎቹ (ባርባሪያንስ) በመደጋገም ስለተወረረችና በመጨረሻ በስፔን ከተቃጠለች በኋላ ታላቋ የሮማ መንግሥት ግባ ከመሬት ውድቀት ደረሰባት። የታላቋ የሮማ መንግሥት ፍጻሜ ይህ ሆነ።

ከሮማ መንግሥት ውድቀት በኋላ የኢጣሊያ ሕዝብ ተከፋፍሎ ለአንድ ሽህ አምስት መቶ ዓመታት ገደማ የውስጥና የውጭ ኃይሎች የጦር አውድማ ሆኖ ኖረ። መንግሥቱ አልቀጠለም። የአክሱም ውድቀት የሮማ መንግሥት ውድቀት ዓይነት ይምሰል እንጅ ከአክሱም ጀምሮ ተያይዞ የመጣው የነገሥታት መንግሥት ቀጥሏል። የአክሱም መንግሥት የወደቀው በፈላሽዋ ንግሥት በ”ዩዲት” አክሱም ከተቃጠለች በኋላ መሆኑ ከሮማ መንግሥት ጋር ይመሳሰላል። በዚህ የአክሱም ዘመን ትግረኛና አማርኛ ተናጋሪዎች መኖራቸው አልታወቀም።

አማርኛና ትግርኛ ከመንደር የወጣ ቋንቋ አይመስልም። የአክሱም ቋንቋ ከመንግሥቱ ውድቀት ጋር የተያያዘ ስለነበር ከመንግሥታዊ ቋንቋ ወደ ቤተ ክርስቲያን ቋንቋ ተዛውሮ እስከዛሬ ድረስ ቤተክርስቲያንን ያገለግላል።  የሮማዊያኖቹ  ቋንቋ “ላቲን”ም ። የሆነው ከመንግሥታዊ ቋንቋ ወደ ቤተ ክርስቲያን መዞር ነው። “ሮምና አክሱም” የወደቁት ብዙ በማይራራቅ ክፍለ ዘመን ሲሆን ከአክሱም ነገሥታቶች ጀምሮ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ የነገሱት ነገሥታቶች ወደ ፫፻ (ሶስት መቶ) አጼዎች ግዕዝ ተናጋሪዎቹም ሆኑ አማርኛ ተናጋሪዎች የዘራቸው መሠረት አክሱም ነው። በዚህ ምክንያት እስከ አጼ ተወድሮስ ዘመን ድረስ ነገስታቶቹ “ዘውድ፡ የሚደፉት አክሱም ፅዮን እየሄዱ ነበር።

ከአጼ ተወድሮስ እስከ አጼ ኃይለሥላሴ የነገሡት ነገሥታቶች ከአጼ ዮሐንስ በቀር ዘውድ የደፉት ከአክሱም ውጭ በጎንደር፤ በአዲስ አበባ ነበር። ይህም የሆነበት በዘመኑ ጽጥታ ስላልነበር ነው። በአክሱም ከአንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን (መክዘ) ጀምሮ ነገሥታቶቹ ሲጠሩበት የነበረው “የመናዊው” ወይም ”ሳባዊው” አጠራር “ሙካሬቭ” የሚባለው ስያሜ ቀርቶ “ንጉሠ ነገሥት” የሚባለው መጠሪያ ለሁለት ሺህ ዓመት ገደማ የነገሥታቱ መጠሪያ ሆኖ ኖሯል። ይህ የታሪካችን ሂደት የተጠቀሰበት ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ መሠረቱ አንድ መሆኑንና በትግረኛና በአማርኛ ተናጋሪዎች ከቋንቋ በቀር ልዩነት እንዳልነበረ ለማሳየት ነው። ሌላውን ብሄር ኦሮሞ፤ ጉራጌ፤ ሲዳማ፤ ወላይታን፤ አፋርን ወዘተ… ታሪኩ ይጨምራል።

ወያኔዎች አማርኛ ተናጋሪዎችን ከምድረ ኢትዮጵያ ለማጥፋት ወይም ከመሬት ላይ የቆሙ ነፍስ የሌላቸው በድን ለማድረግ ያደረጉትና የጣሩት ምንም የተጨበጠ ምክንያት ሳይኖራቸው በተራ ምቀኝነትና ጥላቻ ነው። ለምን የአማርኛ ተናጋሪዎችን እንደጠሉ ምክንያታቸውን ዘርዝረው ማስረዳት ይኖርባቸዋል። በጠቅላላ ሠላሳ ሚሊዮን የአማራ  ሕዝብ ወንጅለዋል። ከወያኔ ብቻ  የፈለቀ የኋላ ቀርነት አስተሳሰብ ነው። ሕዝብ ጥሩም አይደለም፤ መጥፎም አይደለም። ሕዝብ ነው። በሕዝብ ውስጥ ብዙ አይነት የህብረተሰብ ክፍል አለ። ህጻን፤ ሽማግሌ፤ አሮጊት፤ የተማረ፤ ያልተማረ፤ ደግ፤ ክፉ መነኩሴ፤ ሼክ፤ ሽፍታ፤ ሌባ፤ ነፍሰ ገዳይ፤ ጀግና፤ ባንዳ፤ .. ወዘተ ያቀፈ ነው። ሕዝብን ወደ መጥፎ መንገድ የሚመሩትና የሚያሠሩት መሪዎቹ ናቸው;፡ የጀርመን ህዝብ መጥፎ ሆኖ አይደለም፤ ግን በሂትለር የጥላቻ አስተሳሰብ ስለተመራ ከፍተኛ እልቂት በአውሮፓ አስከትሏል። ኢትዮጵያ የሚሆነውም እንደዚሁ ነው። የወያኔ መሪዎች እንጅ  የተወለደበት አገር ሕዝብ አይደለም። በሕዝቡ ስም ግን የአማራን ጥላቻም ሆነ ብዝበዛ፤ ዘረፋ፤ ግድያ፤ ማሠር፤ መግረፍ፤ የጎንደርን፤ የወሎ፤ የአፋርን አገር ቆርሶ መውሰድ፤ የአዲስ አበባን መሬት፤ ኑዋሪውን ሕዝብ ቀምተው የራሳቸውና የደጋፊዎቻቸው በማድረግ ሃብትና ንብረት በመዝረፍ ይጠቀሙበታል።

የዎያኔ የአማራ ጥላቻ መጥፎ በሽታ ስለሆነ አዕምሮውን ዘግቶታል። ዐይኑ እንዳያይ፤ ጆሮው እንዳይሰማ አድርርጎታል። አአምሮውን ጥሩ ከማሰብ ወደ መጥፎ ማሰብ ለውጦታል። ሩህሩህና አዛኝ የአእምሮና  የእጅ ለጋሽ ለኢትዮጵያ አየር፤ውሃ፤ መሬቱ የማያስብ፤ በገንዘብ ፍቅር ብቻ ተቀስፎ የተያዘ አገርና ሕዝብ የማይወድ ባንዳ እንዲሆን አድርጎታል።

ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው በአማራ፤ በጉራጌ ጥላቻ፤ በኦሮሞ ንቀት ምክንያት ነው። ይህን ክፉ ሥራ በሕዝብ ላይ የሚፈጽመውና ኑሮውን የሚበውዘውና እርስ በርሱ በጠብ እንዲኖር የሚያደርገው የተወለደበትን አገር ሕዝብ መከታ አድርጎ ነው ቢባል ስህተት አይመስለኝም። ይህን በገሃድ፤ በግልጽ “ወያኔ ትግራይ፤ ትግራይ ወያኔ” ብሎ አውጇል። በሱ ላይ የተነጣጠረውን ሁሉ በትግራይ ሕዝብ ላይ እነተነጣጠረ አድርጎ ሕዝቡ እንዲደግፈው ጥረት አድርጓል። ይህ ማለት ግን ሕዝቡ በግልጽ ወጥቶ ባይናገርም ሁሉም ይደግፈዋል ማለት አይደለም። ይሁንና የሚደግፈውም ሆነ የማይግፈው የትግራይ ሕዝብ፤ በተለይ በውጭ የሚኖረው በግልጽ “ይህን ክፉ ሥራህን አቁም፤ በኛ ሥም ቁማር አትጫወት” ሊለው ይገባል።

የአጼ ኃይለሥላሴንም ሆነ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን መንግሥት ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ተባብሮ የጣለው እኮ አማራው ነው – ከትግራይ፤ ከኦሮሞ ከጉራጌ ፤ ወዘተ ሕዝብ ጋር ሆኖ። የአማራ መንግሥት ናቸው ብሎ ዝም አላለም። ወያኔ አማራን ያዋረደ መስሎት “ትምክህተኛ፤ ነፍጠኛ” የሚል ስም ሰጥቶታል። ሁለቱም አማራ ሊያፍርባቸው የማገባ ቅጽሎች ናቸው። “ትምክህተኛ” የማይልከሰከስ፤ ኩሩ፤ በራሱ የሚተማመን ልበ ሙሉ ማለት ሲሆን፡ “ነፍጠኛ” ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅነት የሀገሯን ደንበር የጠበቀ፤ ከውጭ ጠላት ጋር በጦር አውድማ የተሰዋ ማለት ሲሆን፡ ለዚህ ኦሮሞውም፤ ትግሬውም፤ ጉራጌውም፤ ሲዳማውም፤ ወዘተ .. አስተዋጻኦ አድርጓል። ወያኔና ተከታዮቹ ሆድሞች፤ “ትምክህተኛ፤ ነፍጠኛ” የሚሉት ሕዝብ የኢትዮጵያን የባህር በር አልዘጋም። መሬቷን ቆርሶ ለፖለቲካ ጥቅም አልሸጠም። ለኢትዮጵያ ነጻነት የሞተ ሀገሩን የሚወድ ሕዝብ ነው። ሕዝቡን እየዘረፈ ሃብትና ንብረት አላካበተም። በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር አላሸሸም። ለገንዘብ የኢትዮጵያን ወታደር ደም ”መርሰነሪ” ሆኖ አልሸጠም፤ ዘረኛ አይደለም። “ሰው ባያይ እግዚአብሄር ያያል” የሚል ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያን ቡናና ወርቅ እየሠረቀ ወደ ውጭ አላከም። እንደወያኔ ኪርይ ሰብሳቢ ነጋዴ መንግሥት አልነበረም። በአዲስ አበባ ከተማ ከሕዝብ በተቀማ መሬት፤ በሕዝብ ገንዘብ በጉቦ በሺዎች የሚቆጠር ፎቅና ቤት ገንብቶ ኪራይ አልሰበሰበም። ኑዋሪውን የአዲስ አበባ ሕዝብ አልበተነም። የመንግሥታቸው አወቃቀር በሲቪሉም ሆነ በወታደሩ ከትግሬው፤ ከአማራው፤ ከኦሮሞው፤ ከጉራጌው፤ ወዘተ… የተውጣጣ ሁሉን አቀፍ እንጅ በዘረኝነት የተዋቀረ አልነበረም። ከወያኔና ከሆዳም ደጋፊዎⶫቸው ጋር ሲነጻጸር በእውቀት፤ በአስተዳደር፤ ችሎታ፤ በሞራል ብቃት፤ ለሕዝብ በነበራቸው ፍቅር የበለጡ ነበሩ ማለት ይቻላል፤ በተለይ የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት።

በአጼ ኃይለሥላሴም ሆነ በመንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት እንኳን ሲቪሉንና ወታደሩ፤ ነጋዴው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደነበረው አልሰማነም። አልተጻፈም። የሕዝብ ገንዘብ መዝረፍ አሳፋሪ፤ ነውር መሆኑ የገባቸው ነበሩ ማለት ይቻላል።

ይህ ጸሃፊ የሁለቱ መንግሥታት ተቃዋሚ እንጅ ደጋፊ አልነበረም። ስለሁለቱ ጥፋታቸውን በመዘርዘር ይጻፍ እንጅ፤ የሕዝብ ገንዘብ በመዝረፍ፤ በዘረኛነት ሕዝብ በማሰቃየት (በተለይ የአጼ ኃይለሥላሴን መንግሥት) አልወነጀላቸውም።

ለመሆኑ ወያኔ ከድሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፈውን ሃብት መቸና እንዴት የት ሊጠቀምበት ያስባል? ወደ ውጭ ልኮ በተለያይዩ ባንኮች ያካበተውን ብር ወለድ የሚበላው መቸ ነው? ዘጠና አምስት ፐርሰንቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት ጦሙን እያደረ ወያኔ እስከ ሆዳም ደጋፊዎቹ (አማራው፤ ኦርሞው፤ ወዘተ.) ጠግቦ ይኖራል የሚል ህልም አለው?፧ ምግቡ ይስማማዋል፤ እርግጠኛ ነኝ። ሰው እንደመሆኑ መጠን የሚሠራው ሃጢያት ሁሉ የሰላም እንቅልፍ እንደማያስተኛው፤ ሲቃዥ፤ በነጭ ላብ ተጠምቆ እንደሚያድር አልጠራጠርም። እንኳን ይህ ሁሉ ክምር ሃጢአት ሰው ሆኖ ለተፈጠረ ትንሽ ውሸት እንኳ እንቅልፍ ትነሳለች። ወያኔ በዚህ ምክንያት በዚህ ዓለም እስከኖረ ድረስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸመውና የሚፈጽመው ወደር የሌለው ወንጀል ቀንም ሆነ ሌሊት እንደሚከነክነው አልጠራጠርም። ሃብትና የአባቶቻቸውን ታሪክ የሚወርሱት ልጆቻቸውም ይህን አብረው ይወርሳሉ።

በፒዲኤፍ ለማንበብ እዚህ ላይ እዚህ ላይ ይጫኑ