This post was published on Sunday, June 24th, 2012 at 11:12 and is filed under Read Amharic.

ኢትዮጵያ በአይምሬው የሙስና ቫይረስ ተጠቅታለች

ከአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ የተሻለች ናት እያልን ስናስተጋባ ብንቆይም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ የምትኮራበት ደረጃ ላይ ሳይሆን የምታፍርበትና የምትሰጋበት አደገኛ የሙስና ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በአይምሬው የሙስና ቫይረስ ከተጠቃች ለሕይወትዋም አስጊ ነው፡፡ በመጀመሪያ አንድ ዓቢይ ነጥብ ግልጽ እናድርግ፡፡ በመንግሥት መሥርያ ቤቶች በሠራተኛ፣  በሹመኛ፣ በከፍተኛ ባለሥልጣናትና በሚኒስትርነት ደረጃዎች ንፁኃንና ቅን ሰዎች አሉ፡፡ ስለሙሰኞቹ ስናወራ ንፁኃንና ቅኖች፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ቀና ደፋ የሚሉና ፀረ ሙስና ኃይሎች የሉም እያልን አይደለም፡፡ ንፁኃንና ቅን የሕዝብ አገልጋዮች አሉ፡፡ ነገር ግን በሙሰኞች እየተሸፈኑ፣ እየታፈኑ፣ እየተረገጡ፣ እየተገፉ፣ እየተባረሩና እየተሸማቀቁ የበላይነትን የያዘ መልካም ባህርይ በሥራ ላይ ሊያሳዩ አልቻሉም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሙስና በሁሉም የመንግሥት መሥርያ ቤቶችና በሁሉም ክልሎች ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ ከመንግሥት ተቋማት ውጭ በግል ዘርፉም ተዛምቷል፡፡ በሲቪል ማኅበረሰቡ ውስጥ አለ፡፡ በሚያሳዝንና በሚያሳስብ ሁኔታም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥም እየታየ ነው፡፡

ከባንኮች ብድር ለማግኘት በመቶኛ ጉቦ እየተጠበቀ ነው፡፡ ለማስገመትም እንደዚሁ፡፡ በመሬት ጉዳይ ጉቦ አንቀሳቃሽ ኃይል እየሆነ ነው፡፡ በጨረታ ለማሸነፍና ጨረታ ለማሰረዝ፣ ለማስለወጥና ለማስረዘም ሙስና መሪ ተዋናይ እየሆነ ነው፡፡ የሥራ ዕድል ለማግኘት ሙስና ይተውናል፡፡ በሹመትና በዕድገት ላይ ሙስና ቅመም ነው፡፡ ድሮ ጉቦና ንቅዘት እየተባለ ይጠራ የነበረው ‹‹ሙስና›› የሚለውን መጠሪያ ከያዘ ወዲህም ጥፋቱ ጋብ ሊል አልቻለም፡፡ እንዲያውም ብሶበታል፡፡ በሙስናም መተካካቱ ቀጥሏል፡፡

ሙስናው በስፋት እንደሚሰራጨው ‹‹አተት›› (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) ሆኗል፡፡ እየሆነም ነው፡፡ ‹‹ኦአርኤስ›› ሊገኝለትም አልተቻለም፡፡ ሙስና በግዕዝ ፍቺው ‹‹ጥፋት›› የሚለውን ትቶ አዲሱ መገለጫ ሙስና (ውበት) የሚለው ተተካለት ወይ ያሰኛል፡፡

በሃይማኖት ተቋማትም ጉዳይ ለማስፈጸም በተዋረድ አቤቱታ አቅራቢ ደጅ ጠኚዎች ጉዳያቸውን ለማወቅ ሲጠይቁ ለመሆኑ የሃይማኖት ሚስጢሮችን ታውቃለህ? አምስቱን፣ ሰባቱን፣ ዘጠኙን ሚስጢሮች ታውቃለህ ይባላሉ፡፡ ጥያቄው በ‹‹ሰሙ›› የሚታወቀውን የሃይማኖት ትምህርትን ለማመልከት ሳይሆን በ‹‹ወርቁ›› አምስት ሺሕ፣ ሰባት ሺሕ፣ ዘጠኝ ሺሕ ብር በእጅ ማለት አለብህ ማለት ነው፡፡ ካልሰጠህ ጉዳይህ አይፈጸምልህም ቦታም አታገኝም ነው፡፡ በሁሉም ሃይማኖቶች እየታየ ያለው፡፡

የሙስና ስፋትና አደጋ አይታወቅም እንዳይባል ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራሳቸው በግሉ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ውስጥም የመንግሥት ሌባ አለ ብለዋል፡፡ ትክክል ነው፡፡

መነሳት ያለበት ጥያቄ ግን በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሌባ እንዳለ ከታወቀ ሌባውን ለማስወገድ ለምን ዕርምጃ አይወሰድም? ነው፡፡ ከጥያቄው ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሌላው አሳሳቢ ጥያቄም መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት አቅም አጥቷል ወይ? የሚል ነው፡፡ መንግሥት እጁን ሰጥቷል ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡

ይህ ጥያቄ  ሊነሳ የሚችለው አንዳንዱ በሙስና ተከሶ ፍርድ ቤት መቆም ሲገባው፣ ተሹሞ በል ቀጥል መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ ሲባል እየተስተዋለ ነው፡፡ ሠርቶ አደሩን ያበረታታሉ የተባሉ ‹‹ሰርቆ አደር›› ሆነዋል፡፡ የአርሶ አደሩን ችግር ይፈታሉ የተባሉትም ‹‹አስርቦ አደር›› እየሆኑ ናቸው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሀቅ ይዞ መኖር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሕግን ተማምኖ መኖር የትም የማያስኬድ እየሆነ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገርንና ሕዝብን ለመጥፎ ጉዳት እየዳረገ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሞላጫነት፣ ሙሰኝነት፣ አጭበርባሪነት፣ ግለኝነት፣ ክህደት፣ ውሸትና አስመሳይነት የማቴሪያላዊ ጥቅም አስተማማኝ ዋስትና ወደሆኑበት ሥርዓት እየተሸጋገርን ነን፡፡
መልካም አስተዳደር ሲባል የነበረው ራዕይና ግብ የት ገባ?

ከምንለው ችግር ሁሉ በላይ ከሙስና ቫይረስ ጋር የተያያዘ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በኢትዮጵያችን እየተከሰተ ነው፡፡ የማፍያ ኃይል በእጅጉ እየተጠናከረ ነው፡፡ የማፍያ ቡድኖች እየተበራከቱ ናቸው፡፡ በእርግጥ የማፍያ ቡድኖቹ ደረጃ አንድ፣ ደረጃ ሁለት፣ ደረጃ ሦስት፣ ደረጃ አራት እያልን በገንዘብ አቅም፣ በሰው ኃይል ብዛትና ባላቸው አደረጃጀት፣ ስፋትና ጥልቀት ልንመድባቸው እንችላለን፡፡ ቁምነገሩ ግን ሁሉም ማፍያ እስከሆኑ ድረስ ሕግ አያከብሩም፣ ያስፈራራሉ፣ በገንዘብ ይገዛሉ፣ የበላይነት ለመያዝ ይጥራሉ፣ በመጨረሻው ግባቸው ከተሳካ አገር ይገዛሉ፣ ይሸጣሉ፣ ይለውጣሉ፡፡ ‹‹በሊዝ›› ሳይሆን ለዘለዓለሙ፡፡

መንግሥትም፣ ሕዝብም፣ መገናኛ ብዙኃንም፣ ምሁራንም፣ የግል ዘርፉም፣ ሲቪል ማኅበረሰቡም፣ ወጣቱም፣ ሁሉም በጋራ ሙስናን ለመዋጋት ዘብ ይቁም፡፡ በተጠንቀቅ!

ኢትዮጵያ ከተጎዳች፣ ከተሸጠች፣ ከተለወጠችና ከሞተች በኋላ ቀብር፣ ሐዘን፣ እዝን፣ ሰልስት እያልን ብንወራጭ ትርጉም የለውም፡፡ ከአደጋው በፊት እንረባረብ፡፡
አደጋው ግልጽ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአይምሬው የሙስና ቫይረስ ተጠቅታለች፡፡