ክርስቲያኑ ማህበረሰብ ከሙስሊሙ ጋር እንዲተባበር ጥሪ ቀረበ

እስላሙም ወገናችን ክርስቲያኑን በመደገፍ፤ ክርስቲያኑም ወገናችን እስላሙን በመደገፍ ሁሉም እንዲነሳና ድምጹን እንዲያሰማ ጥሪየን አቀርባለሁ” ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መልከጸዲቅ

33ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. May 12, 2012)፦ በስደት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ የሆኑት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መልከጸዲቅ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እደረሰ ያለውን አስከፊ ጭፍጨፋ በማውገዝ መላ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት ተከታዮች ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላለፉ።


ከሶስት ቀናት ጉባኤ በኋላ ዛሬ የተጠናቀቀው 33ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመከረ በኋላ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ ያደረገ ሲሆን በተለይ በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ መንግስት እያደረሰ ያለውን ግድያና እንግልት በማውገዝ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ኃይማኖት ተከታይ ክርስቲያን ማህበረሰብ ከሙስሊም ወንድሞችና እህቶች ጎን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፏል።


በሀይማኖት ውስጥ ህገወጥ በሆነ መልኩ ህወሃት/ኢህአዴግ ሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ያወገዙት የህጋዊው ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መልከጸዲቅ ለኢሳት እንደገለጹት “ቤተ ክርስቲያን ተበደለች፤ ቤተ ክርስቲያን ተገፋች ብለን ተሰደን ነበርን። ለጊዜው ይዋል ይደር እንጅ ወንድሞቻችን እስላሞችም ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በመሆናቸው እየተገፉ፤ እየተበደሉ ነው የሚገኙት። ስለነሱም ቢሆን ቤተ ክርስቲያን ትጮሀለች። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ናቸውና። በሀይማኖታቸው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን በመሆናቸው የእኛ እድል እየገጠማቸው ነው።” ያሉት አቡነ መለረከጸዲቅ በማከልም “ እስላሙም ወገናችን ክርስቲያኑን በመደገፍ፤ ክርስቲያኑም ወገናችን እስላሙን በመደገፍ ሁሉም እንዲነሳና ድምጹን እንዲያሰማ ጥሪየን አቀርባለሁ” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።


ቅዱስ ሲኖዶሱ ሰሞኑን ከፍተኛ ውጥረት የነገሰበትን የዋልድባ ገዳምን መደፈር እና ወቅታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ውይይት ያደረገ ሲሆን ውሳኔውንም በመግለጫው ማካተቱን ለማወቅ ችለናል።


በተያያዘ ዜና በአባ ጻውሎስ የሚተዳደረውና በአብዛኛው የኃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ተቀባይነት ያላገነው ሲኖዶስም በአዲስ አበባ ላለፉት ሶስት ቀናት ጉባኤ የተቀመጠ ሲሆን በተለይ በአቡነ ሳሙኤልና በአቡነ ጳውሎስ መካከል ፍጥጫው መቀጠሉንና አቡነ ጳውሎስ በሰባት ወራት ውስጥ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ከኮሚሽኑ መጠየቃቸው የተወሳ ከመሆኑም በላይ ከውጭ ሀገር በስደት ከሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ያለውን የእርቅ ሂደት በሚመለከት የቀረበውን አጀንዳ የተቃወሙት አባ ጳውሎስ ከተላኩት ጳጳሳት መሀከል አንዱ “ወደኋላ ቀርተው ከእነርሱ ጋራ ነገር ሲሸርቡብኝ ነበር” በማለት ከሰው የእርቅ ሂደቱን እንደማያምኑበት ቢገልጹም አብዛኛው የሲኖዶሱ አባላት የሆኑ አባቶች ግን  “በእኛ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ አትቀርም፤ ለቀጣዩ ትውልድ ለሁለት የተከፈለች ቤተ ክርስቲያን ማስረከብ አንሻም፤ የዕርቅ ሂደቱ መቀጠሉ ግድ ነው፤ በእግራችንም ቢኾን እዚያው ሄደን እናሳካዋለን” ሲሉ በድፍረት ምለሽ መስጠታቸውን ደጄ ሰላም ዘግቧል።


ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መልከጸዲቅ ከጉባኤው በኋላ የሰጡትን መግለጫ ለመመልከት የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!


FacebookTwitterGoogle+Share

Share this post:

Related Posts

ZONE 9 BLOGGER PARADISE IN ETHIOPIA

Leave a Comment