ከዚህ በሁዋላ ከጳውሎስ ጋር አብረን አንሠራም
ከደጀ ሰላም:
• “ከዚህ በሁዋላ ከከጳውሎስ ጋር አብረን አንሠራም” ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፤ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ
• “ሀገረ ስብከቴን ተረከቡኝ” ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣
• ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ያልተጠበቁ የፓትርያርኩ ደጋፊ፣
• ፓትርያርኩ “ተቃዋሚዎቻቸውን ይበቀላሉ” ይባላል፣
• አቡነ ሳሙኤልን ስላገቱት ሰዎች ፌዴራል ፖሊስም አያውቅም፣
ቅዱስ ሲኖዶሱ ያረቀቀውን ቃለ ጉባዔ ሳያጸድቅ፣ የጀመረውን አጀንዳ ሰይቋጭ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሜዳ ላይ ጥሎ ወደ ቤቱ ገብቷል። ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ውሳኔ በፊርማ እንዳይጸድቅ ብፁዓን አበው እስጢፋኖስ፣ ኤጲፋንዮስና ጎርጎርዮስ የሞት ሽረት ትግል አድርገው፣ አባቶችን በጥብጠው ውሳኔው እንዲከሽፍ አድርገዋል። በተለይም በምዕራብ ኢትዮጵያ በጀመሩት መልካም አገልግሎት በሕዝቡ እየተመሰገኑ የነበሩት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ይህንን ገዳይ አቋም እንዴት ሊይዙ እንደበቁ እንቆቅልሽ ሆኗል። ገሚሱ በገንዘብ ተገዝተው ነው ሲል ሌላው ደግሞ ውስጠ ዘ በሆነ ማስፈራሪያ ሊሆን ይችላል እያለ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ አሸናፊነቱ እየመጡ ያሉት ፓትርያርኩ የበቀል በትራቸውን እንደሚመዙ እየተጠበቀ ነው። የመጀመሪያ ተጠቂዎች የሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት በብፁዕ አቡነ ሳሙኤል መሪነት ስብሰባ ካደረጉ በሁዋላ የፓትርያርኩን ድርጊት የሚቃወም መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል። ከዚህም ባሻገር ይህንን ሁሉ ሕዝብ ያስተባብርብኛል ያሉት ማህበረ ቅዱሳንም ላይ ጥርሳቸውን ነክሰዋል ተብሏል።
የቤተ ክህነቱ ድራማ ዛሬ ሲተወን ጠዋት በማለዳው ስብሰባ እንዳይገቡ የታገቱት ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ለምን እንደታገቱ ፌዴራል ፖሊስ ራሱ አያውቅም። የደህንነት ክፍሉ ደግሞ ለደህንነታቸው ብዬ ነው ብሏል። ድራማው ሊቀ ጳጳሱን ከስብሰባው በማስቀረት ውሳኔውን ማክሸፍ ከሆነ በርግጥም ዘዴው ሰርቷል ማለት ይቻላል።መንግሥት በበኩሉ ጉዳዩን እያጠናው እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና ፓትርያርኩ የተነሣባቸውን ተቃውሞ ለመስበርና አባቶችን አንገት ለማስደፋት የሚሆን ገንዘብ ራሳቸው በግላቸው ከሚያዙበት ከቁልቢ ገብርኤል ካዝና ወጪ መደረጉ ታውቋል። የብሩ መጠን ለጊዜው ባይታወቅም ገንዘቡ ለአንዳንድ የፖሊስ ሃላፊዎች፣ ደህንነቶችና ጉልበት ላላቸው ሰዎች መበተኑ ሲታወቅ መንግሥት በውስጡ ሌላ መንግሥት ያለበት አስመስሎታል። እስከ ዛሬም በመንግሥት ስም ቤተ ክርስቲያኒቱን እግርተወርች አስረው ሲበሏት፣ ሲግጧትና ሲያዋርዷት የነበሩ ሰዎች የፓትርያርኩ ዘመዶችና ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተንፈራጠጡ ሰዎችም መሆናቸው እየተገለጸ መጥቷል። መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ ሕገ ወጦቹ እጃቸውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እንዲያነሱ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል።
ነገሩ በዚህ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ አላት ለማለት እንደማያስደፍር አንድ ሊቀ ጳጳስ ተናግረዋል። ከዋሺንግተን ዲሲ ተጠርተው የተሾሙት የሲዳሞ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሥራ አስፈጻሚው አባል ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልም በበኩላቸው “ሀ/ስብከቴን ተረከቡኝ” ማለታቸው ተሰምቷል። በርግጥም ሊቀ ጳጳሱ እንዲህ ካደረጉ ጳጳሳት የሥራ መልቀቂያ የሚያስገቡበት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ሳይሆን በፓትርያርክና በሴት ወይዘሮዎች ብቻ የሚመራ ቤተ ክህነት ይፈጠራል ማለት ነው።





































![Must Read Book: Ethiopia – Tiwoldena Kirsu [A Generation and Its Heritage]](http://www.ethiosun.com/wp-content/uploads/2010/02/Book_edited-21.png)



















